ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በ20 ቀናት ሁለት ጊዜ ኮሮና የተገኘባት ስፔናዊት በአጭር ጊዜ ዳግም በቫይረሱ የተያዘች ሳትሆን አትቀርም ተባለ
የ31 ዓመቷ የጤና ባለሙያ በ20 ቀናት ውስጥ ሁለት ጊዜ በኮሮና ቫይረስ እንደታያዘች ተገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ በቫይረሱ ሁለት ጊዜ በመያዝ የታወቀ አጭሩ ጊዜ ነው ሲሉ የስፔን ተመራማሪዎች ገልጸዋል።
ባለሙያዋ በሃያ ቀናት ውስጥ ዴልታ እና ኦሚክሮን በተባሉ ሁለት የኮቪድ ዝርያዎች መያዟ ነው የተረጋገጠው።
ታዲያ ይህ ሁኔታ አንድ ሰው በቫይረሱ ቀደም ብሎ ቢያዝም ሆነ ሙሉ በሙሉ ክትባቱን ቢወስድ ዳግም በቫይረሱ ሊያዝ እንደሚችል ያመላከተ ነው ሲሉ ተመራማሪዎች ገልጸዋል።
በዩኬ ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ ዳግም ለመያዝ ቢያንስ 90 ቀን እንደሚፈጅ ታውቋል።
በዚህ እሳቤ መሰረት በሀገሪቱ 900 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በዚህ ወር መግቢያ በቫይረሱ ዳግም የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ የጤና ዘርፉ ባለስልጣናት አሳውቀዋል።
በላብራቶሪ ባለው ሂደት እና የሚወሰደው ናሙና ጥቂት በመሆኑ በቫይረሱ ዳግም የተያዙ ሰዎችን ትክክለኛ ቁጥር ለመያዝ አዳጋች ነው።
በሃያ ቀናት ልዩነት በቫይረሱ የተያዘችው ስፔናዊት በቫይረሱ እንደተያዘች ካረጋገጠች በኋላ ምንም ዓይነት የኮሮና ምልክቶች አልታዩባትም ነበር።
ሆኖም ግን ከሶስት ሳምንታት በነሳ ጊዜ ውስጥ የቫይረሱን ምልክቶች በማየቷ ድጋሚ ለመመርመር ምክንያት ሆኗታል። በውጤቱም ቫይረሱ እንደያዛት የተረጋገጠ ሲሆን ከመጀመሪያው የተለየ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ሁለተኛው ምርመራ ላይ ተገኝቷል።
በአውሮፓ ውስጥ በሚገኝ አንድ የህክምና ምርምር ተቋም ጉዳዩን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት ዶክተር ጄማ ሪሶ ይህ ሁኔታ ኦሚክሮን ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ በተፈጥሮ የሚያዳብሩትን ወይም በክትባት የሚያገኙትን በሽታ የመከላከል አቅም እንደሚበግር የሚያሳይ ነው ብለዋል።
"በሌላ አገላለጽ በኮቪድ 19 ተይዘው የነበሩ ሰዎች ክትባቱን ሙሉ በሙሉ ቢወስዱ እንኳን ለቫይረሱ አንጋለጠም ብለው ማስብ አይችሉም" ሲሉ አስረድተዋል።
ሆኖም ግን በቫይረሱ ቀድሞ መያዝ እና ክትባቱን መውስድ ከከፍ ህመም እና ሆስፒታል ከመግባት ሳይታደግ አይቀርም ሲሉ አክለዋል።
ተመራማሪዋ ክትባት ሙሉ በሙሉ ወስደው በቫይረሱ ዳግም የሚያዙ ሰዎች ላይ የሚደረገው ምርመራ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው የኮቪድ ዝርያዎች ለክትባት ያላቸውን አይበገሬነት ለማጥናት ይረዳል ብለዋል።
በዓለም ዙሪያ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ዳግም እንደተያዙ የሚያመላክቱ ቁጥሮች ከፍ ያሉት ኦሚክሮን የተባለው ዝርያ መገኘቱ ከታወቀ በኋላ ነው። በሌላ በኩል ባለፈው ወር ቢኤ 2 የተባለው የኮሮና ዝርያ መገኘቱን ተከትሎ በቫይረሱ ዳግም የሚያዙ ሰዎች ተበራክተዋል።
ይህ ዝርያ ከመገኘቱ በፊት በዩኬ ለሁለተኛ ጊዜ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 1 በመቶ ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን ወደ 11 በመቶ አሻቅቧል።
አብዛኞቹ ሰዎች ቀደም ብሎ አልፋ ወይም ዴልታ በተሰኘው ቫይረስ ተይዘው የነበረ ሲሆን ለሁለለተኛ ጊዜ ሲያዙ የተገኘው ኦሚክሮን ዝርያ ነው።
በዚህም መነሻ ማንኛውም ሰው በቫይረሱ ሁለት ጊዜ ሊያዝ እንደሚችል እና በህይወት ዘመን ውስጥ ከሁለት ጊዜም በላይ የመያዝ እድል እንዳል ሳይንቲስቶች ግምታቸውን አስቀምጠዋል።