የሩሲያ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ምልመላ ይካሄዳል መባሉን ውድቅ ማድረጉን መንግሥት አወደሰ

ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በምታደርገው ጦርነት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች እየመለመች ነው የሚለውን ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች የሩሲያ ኤምባሲ ውድቅ ማድረጉን የኢትዮጵያ መንግሥት በመልካም ጎኑ እንደሚቀበለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ኤምባሲው ምንም አይነት የውትድርና ምልመላ ማመልከቻን እንደማይቀበልና የአውሮፓውያኑን 1961 የቪየና ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ስምምነት እንደሚያከብር መግለጹን አስታውሷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲህ አይነት የውትድርና ምልመላዎች በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ያለውን የቪየና ስምምነትን የሚጻረርና የዲፕሎማቲክ ተልዕኮም ጋር የሚጣረስ መሆኑን ስለሚያምን አቋሙ ከኤምባሲው ጋር ተመሳሳይ ነው ብሏል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ ፌዴሬሽን ኤምባሲ በትናንትናው እለት ሚያዚያ 11/2014 ባወጣው መግለጫ ምንም አይነት የውትድርና ምልመላ ጥያቄዎችን አልቀበልም ብሏል።

ይህ የተባለው "አስፈላጊ በሆነው መንገድ ሁሉ" ከሩሲያ ጎን እንቆማለን ያሉ ኢትዮጵያውያን ከኤምባሲው ፊት ለፊት በብዛት ተሰልፈው መታየታቸውን ተከትሎ ነው።

በኤምባሲው አካባቢ ተዘዋውረው የታዘቡት የቢቢሲ ዘጋቢዎች በርካታ ወጣቶች የተለያዩ ሰነዶችን ይዘው ተሰልፈውና ቆመው ተመልክተዋል።

በኤምባሲው በር ላይ ቆሞ ሲጠብቅ ቢቢሲ ያገኘው ወጣት በጥሩ ደመወዝ በውትድርና ወይም በተገኘው ስራ ለመቀጠር እንደመጣ ተናግሮ፤ "ሩሲያን እወዳታለሁ" ብሏል።

ቢቢሲ ያናገራቸው ሌሎች ግለሰቦች በበኩላቸው በሩሲያ ከፍተኛ ደመወዝ ቅጥር እንዳለ ሰምተናል ብለዋል።

ሚያዚያ 10/2014 ዓ.ም. ላይ ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የኤምባሲው ቃል አቀባይ ማሪያ ቸርኑኪና "አስፈላጊ በሆነው መንገድ ሁሉ'' ከሩሲያ ጎን እንቆማለን የሚሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ኤምባሲያቸው እየመጡ መሆኑን ተናግረው ነበር።

ይኹን እንጂ ኤምባሲው በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ኢትዮጵያውያን ተዋጊዎችን የመመልመል እቅድ እንደሌለው ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤምባሲዎች የተጣለባቸውን የዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ጋር የሚቃረን እንዲሁ እንዲሁም የተቀመጡበትን ሃገራት ህግና ደንብ የማክብር ግዴታ እንዳለባቸው ጠቅሶ እንዲህ አይነት ምልመላዎች በኤምባሲዎች መካሄዳቸው የኢትዮጵያን ህግ ይጥሳል ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኤምባሲው ለወሰደው እርምጃም አድናቆቱን ገልጿል።

ኤምባሲው ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ኢትዮጵያዊያን በአካል እና በኢ-ሜይል በሚልኳቸው መልዕክቶች ለሩሲያ ያላቸውን ድጋፍ እና አጋርነት እየገለጹ ነው ካለ በኋላ፤ ይህ በሁለቱ አገራት መካከል የማይሰበር ወንድማዊ ወዳጅነት ነው ሲል ገልጾታል።

በተመሳሳይ ኤምባሲው ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ፤ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያደረገች ያለችውን ጦርነት የአገሪቱ ጦር በብቃት እንደሚወጣ ባለ ሙሉ እምነት መሆኑን ገልጾ፤ እየቀረቡ ላሉ የአጋርነት ጥያቄዎችም ክብር እንዳለው ገልጿል።

ኤምባሲው በተባበሩት መንግሥታት ሩሲያ በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሩሲያ ያሳየው ድጋፍም የሚደነቅ ነው ብሏል።

ኤምባሲው የ1961 የቬን ኮንቬሽን እንደሚያከብር ገልጾ፤ በዚህ ስምምነት መሠረት የውትድርና ምልመላ በሌላ አገር ማድረግ ተቀባይነት የለውም ብሏል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ በበኩሉ ሚያዝያ 10፣ 2014 ዓ.ም በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ሩስያውያን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ለመልመል ሲሞክሩ እየታየ ያለውን እውነታ አይናገሩም ብሏል።

መግለጫው አክሎም ሩስያ በዩክሬን የመሸነፍ ስሜት ስለተሰማት "በስውር ለማሳሳት እና ቆሻሻ ጨዋታ" ለመጫወት እየሞከረች ነው" ሲል ከስሷል።

ወጣቶቹ ፓስፖርታቸውን ይዘው ቪዛ ለማግኘት የመጡ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ውስጥ በድብቅ ወጣቶችንና ንጹሃን ዜጎችን ለማሰማራት እያሴሩ ያሉ የሩስያ ወታደራዊ ሰላዮችን አላስቆመም ብሏል።