"አስፈላጊ በሆነው መንገድ ሁሉ" ከሩሲያ ጎን እንቆማለን ያሉ ከኤምባሲው ፊት ለፊት ተሰለፉ

ሁለት ወራት ባስቆጠረው የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ከሩሲያ ጎን እንሰለፋለን ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ በሚገኘው የኤምባሲው ደጃፍ በዛሬው ዕለትም ተሰልፈው ይታያሉ።

የቢቢሲ ዘጋቢዎች በኤምባሲው በር ተዘዋውረው እንደታዘቡት በርካታ ወጣቶች የተለያዩ ሰነዶችን ይዘው የካ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው ኤምባሲ ደጃፍ ተሰልፈውና ቆመው ይታያሉ።

በኤምባሲው በር ላይ የሚታዩት አብዛኞቹ ወጣት ወንዶች መሆናቸውን ቢቢሲ ተመልክቷል።

በትናንትናው እለትና ከዚያ በፊት በነበሩት ቀናት ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያደረገች ባለችው ጦርነት "አስፈላጊ በሆነው መንገድ ሁሉ" ከሞስኮ ጎን እንቆማለን የሚሉ ኢትዮጵያውን ከሩሲያ ኤምባሲ በር ቆመው እየጠበቁ ታይተዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች በርካታ ሰዎች "በቅጥረኛ ወታደርነት" ለመመዝገብ በሚል አዲስ አበባ ቀበና ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በር ላይ ተሰልፈው መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በኤምባሲው በር ላይ ቆሞ ሲጠብቅ ቢቢሲ ያገኘው ወጣት በጥሩ ደመወዝ በወታደርነት ወይም በተገኘው ስራ ለመቀጠር እንደመጣ ተናግሯል።

አክሎም "ሩሲያን እወዳታለሁ" ብሏል።

ቢቢሲ ያናገራቸው ሌሎች ግለሰቦች በበኩላቸው በሩሲያ ከፍተኛ ደመወዝ ቅጥር እንዳለ ሰምተናል ብለዋል።

አዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ ፌዴሬሽን ኤምባሲ ቃል አቀባይ ማሪያ ቸርኑኪና "አስፈላጊ በሆነው መንገድ ሁሉ'' ከሩሲያ ጎን እንቆማለን የሚሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ኤምባሲያቸው እየመጡ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገረው የዓይን እማኝ ከትናንት ጀምሮ ረዣዥም ሰልፎችን ኤምባሲው በር ላይ መመልከት መጀመሩን ገልጿል።

ይሁን እንጂ ኤምባሲው በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ኢትዮጵያውያን ተዋጊዎችን የመመልመል እቅድ እንደሌለው ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል።

ማሪያ ቸርኑኪና "እኛ የምልመላ ኤጀንሲ አይደለንም ስለዚህ ተዋጊዎችን አንመለምልም'' ብለዋል።

''በርካቶች የኤምባሲውን ስልክ ስለማያውቁ ወይም ኢንተርኔት ስለሌላቸው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ወደ ኤምባሲያችን እየመጡ ድጋፋቸውን እየሰጡ ነው'' ሲሉም አክለዋል።

ኤምባሲው ከመደበኛው የኮንሱላር ስራዎቹ በተረፈ እንዲህ ያለ ምልመላዎችን እንደማያካሂድ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ በበኩሉ ትናንት ሚያዝያ 10፣ 2014 ዓ.ም በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ሩስያውያን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ለመልመል ሲሞክሩ እየታየ ያለውን እውነታ አይናገሩም ብሏል።

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ዕለት ጀምሮ እስከ ትናንትናዋ ዕለትም ከ20 ሺህ የሚበልጡ "ወራሪ" ብለው የጠሯቸው ሩስያውን ተገድለዋል ብለዋል።

መግለጫው አክሎም ሩስያ በዩክሬን የመሸነፍ ስሜት ስለተሰማት "በስውር ለማሳሳት እና ቆሻሻ ጨዋታ" ለመጫወት እየሞከረች ነው" ሲል ከስሷል።

ወጣቶቹ ፓስፖርታቸውን ይዘው ቪዛ ለማግኘት የመጡ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ውስጥ በድብቅ ወጣቶችንና ንጹሃን ዜጎችን ለማሰማራት እያሴሩ ያሉ የሩስያ ወታደራዊ ሰላዮችን አላስቆመም ብሏል።

ሩሲያ በዩክሬን ወረራ ከፈጸመች በኋላ በተለይ ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ቅጥረኛ ወታደሮችን እየመለመለች እንደሆነ ምዕራባውያን አገራት ክስ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሴኔጋል የሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ የሴኔጋል ዜጎችን ለጦርነት ለመመልመል የቅጥር ማስታወቂያ ማውጣቱ የሴኔጋል መንግሥት የአገሪቱን ህግ የሚጻረር ነው በሚል ኮንኖታል።

እንዲሁም ዩክሬን ጦሯን እንዲቀላቀሉ ለበጎ ፈቃደኞች ጥሪ ማድረጓን ተከትሎ የምዕራባውያን ሃገሮች በጎ ፈቃደኞች ውትድርናን ጨምሮ በተለያዩ ተግባራት ለመሰማራት ወደ ዩክሬን አቅንተዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ የምዕራቡ ዓለም አገራት በሞስኮ ላይ ከፍተኛ የሆነ ማዕቀብ እና መገለል አድርሰውባታል።

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በዚህ ጦርነት አቋሟን በግልጽ ባታሳውቅም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሩሲያን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በሚሰጡ ድምጾች፣ ድምጽ ከመስጠት ስትቆጠብ እና የምዕራባውያንን ውሳኔ ስትቃወም ተስተውሏል።

የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት በተቀሰቀሰ ሰሞን ተዋጊ ኃይሎች የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥበው ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠይቀው ነበር።