ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ጋዜጠኛ አንድ ቡድን በሽብርተኝነት ቢፈረጀም ባይፈረጅም የማነጋገር መብት ሊኖረው ይገባል''
አሚር አማን ገና በህጻንነቱ የከርሞ ሰው በተሰኘው የልጆች የራዲዮ ፕሮግራምን ጨምሮ የቴሌቪዥን እና የልጆች መጽሄቶች ላይ በመስራት ነበር ከመገናኛ ብዙሃን ስራ ጋር የተዋወቀው።
በሚወደው የጋዜጠኝነት ሞያ ለመግፋትም የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በብሮድካስት ጋዜጠኝነት እንዲሁም ወደ ኖርዌይ በማምራት በአለማቀፍ ጋዜጠኝነት የማስተርስ ዲግሪውን ይዟል።
ከኖርዌይ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ ወዲህም ከእንግሊዙ ቻናል ፎር ጋር ለጥቂት ወራት ከሰራ በኋላ በ2013 መጀመሪያ ላይ ለአሶሺየትድ ፕሬስ በዘጋቢነት መስራት ጀመረ።
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በግጭት ቦታዎች ተዘዋውሮ የተለያዩ ዘገባዎችን ከሰራ በኋላ በሕዳር ወር በቁጥጥር ስር ዋለ። አሚር ከአንድ ሳምንት በፊት ከእስር ከተለቀቀ በኋላ በእስሩ ዙሪያ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ቢቢሲ፡ በእስር ላይ መሆናችሁ ሳይሰማ ቆይቶ በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን በተሰራ ዘገባ ነበር በይፋ መታሰራችሁ እንዲሁም "በሽብርተኝነት የተፈረጀ ቡድንን ማስተዋወቅ" በሚል ወንጀል መጠርጠራችሁ የተገለጸው። እስቲ ስለዘገባው ንገረን?
አሚር፡ የተሰራውን ዶክመንተሪ ያየሁት ከተፈታሁ በኋላ ነበር። የአንድን አገር የጸጥታ መዋቅር የሚያስተዳድሩ አመራሮች በዚህ መጠን ዝቅ ብለው የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲከፍቱ ማየት መቼም ያሳፍራል። የመገናኛ ብዙሃኑም ሆነ የፌደራል ፖሊስ ትልልቅ የሕዝብ ተቋማት ሆነው እንደዚህ አይነት ስራ ሲሰሩ ማየት አስቂኝ ነው። ከፈቃዳችን ውጪ ነው የቀረጹን። እንደውም በተለይ እኔ ቃለ መጠይቅ እንድሰጣቸው ፈልገው ነበር። ሃሳቤን ብገልጽ እንኳን ያው እንዴት ተቆራርጦ እና ማለት ያልፈለኩት ነገር እንደሚሰራጭ ይታወቃል፤ ከዚህም በፊት እንደዛ ተደርጎ ስለሚታወቅ።
ስለዚህ እኔ ፈቃደኛ አልነበርኩም። ያለፈቃዴ ቆሜ ሲቀርጹኝ ካሜራ መትቼባቸው ነበር። አለቆቼን እና ጠበቃዬን ማናገር ፈልጋለሁ ስል "እንደማንኛውም ተጠርጣሪ ፎቶህን እንውሰድ" ብለው ነው ያያችሁትን ምስል የወሰዱት።
ዛቻ እና ከዛ የሚያክል ተቋም ሃላፊዎች የማይጠበቅ ስድቦች ነበሩ። የተሰራው ስራ ከኔ በላይ ቤተሰቦቼን እና ጓደኞቼን አስደንግጧል። ያው ይህንን ያደረጉትን ሰዎች እና እነሱ እኛን በሚጠሩን ቃል ከነ ግብረ-አበሮቻቸው እንዴት ተጠያቂ እንደማደርግ ከጠበቆቼ ጋር እየተነጋገርኩ ነው።
ቢቢሲ፡ በስም ማጥፋት ክስ ለመመስረት ሃሳብ አለህ ማለትህ ነው?
አሚር፡ ወደዛም ሊሄድ ይችላል፥ ግን ምን ማድረግ እንዳለብን ከጠበቆቼ ጋር እየተማከርን ነው።
ቢቢሲ፡ አሚር መንግስት ያቀረበብህ ክስ ሽብርተኛ ድርጅትን በአለማቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ሰርተሃል በሚል ነው። ለእስር ያበቃህ ዘገባ ምን እንደነበረ ንገረን?
አሚር፡ እኔ በተለይም በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ አተኩራለሁ። ይህ ደግሞ ነገሮች ከላይ ከላይ ከመዘገብ እና ከማጮህ ይልቅ በጥልቀት የችግሮችን ስር መሰረት በመዳሰስ መፍትሄ መፈለግ ላይ ያተኩራል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ግጭቶች አሉ። እኔም እንደ ምርመራ ጋዜጠኛ እነዚህን ግጭቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ስዘግብ ቆይቻለሁ። ትግራይ፣ አፋር፣ ደቡብ፣ አማራ ክልሎች እንዲሁም በርካታ ቦታዎች በመሄድ ግጭቶችን ከቦታው ዘግቤአለሁ። አሁን ለእስር የዳረገኝ ጉዳይ ምዕራብ ሸዋ በመሄድ የሰራሁት ዘገባ ሲሆን እነሱ የሚሉት "የኦነግ ሸኔ አመራሮችን ቃለ-መጠይቅ አድርገሃል" ነው።
አላደረኩም አላልኩም። አድርጌአለሁ፣ መብት አለኝ ለወደፊቱም እንደዚህ አይነት ዘገባዎችን ለመስራት ፍለጎት ካለኝ ወደ ኋላ አልልም። መረጃ መሰብሰብ እና ማጠናቀር መብት ነው። የራሴን ምርመራ ለማድረግ እና እውነታውን ለማወቅ ይህ ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ከመቼውም ግዜ በላይ የችግሮችን ስር መሰረት ለመረዳት በጥልቀት በእያንዳንዱ ግጭት ላይ ያሉትን ባለድርሻዎች በማናገር መስራት ያስፈልጋል። እኔም ያደረኩት ይህንን ነው።
ጋዜጠኛ አንድ ቡድን በሽብርተኝነት ቢፈረጀም ባይፈረጅም ይህንን የማድረግ መብት ሊኖረው ይገባል። የኔ አላማ ግጭቶቹን ከሁሉም ጎን መዘገብ ነው።
"እኔ ጋር ያለውን ብቻ ጮክ አድርገህ ዘግብልኝ፤ ሌላው ጋር መሄድ አትችልም" ማለት የሚዲያውን ገለልተኝነት እና ነጻነት የሚጋፋ ነው። ደግሞም አንድን ቡድን ማናገር እና ዘገባ መስራት የቡድኑ አባል እና ደጋፊ መሆን አይደለም። እንደሱ ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ አንዳንድ አካላትን እየተከተልኩኝ ዘገባ ስሰራ ነበር። ስለዚህ የእነሱም ደጋፊ ነህ ሊያስብል ነው። ይህ አስቸጋሪ ነው በጣም። የስንቱ አባል ሆነን እንችለዋለን?
በደህንነቶችም ክትትሎች የነበሩ ይመስለኛል። መጀመሪያ እኔን ያዙኝ፣ ቀጥሎ አዲሱን እና ቶማስን በየተራ ያዟቸው።
ቢቢሲ፡ አብረውህ የታሰሩት ጋዜጠኞች የኤፒ ሰራተኞች አልነበሩም። እንዴት ከጉዳዩ ጋር ተያያዙ?
አሚር፡ አዲሱ ዩኒቨርሲቲ አብሮኝ የተማረ ልጅ ነው። የፋና ጋዜጠኛ ነው። ከብዙ አመታት በኋላ ተገናኘን እና የካሜራ ባለሞያ እየቀያየርኩ ስለተቸገርኩ ጥሩ የካሜራ ባለሞያ ፈልግልኝ አልኩት። ከዛም በጓደኞቹ አድርጎ ከቶማስ ጋር ያገናኘኛል። ቶማስ እና አዲሱ አይተዋወቁም፤ እስር ቤት ነው የተገናኙት። አዲሱን ያሰሩት አሚርን ከቶማስ ጋር አገናኝተሃል በሚል ነው። ለጥያቄ ብለው ሁለት ወር ያህል አቆይተው ነው የለቀቁት።
ቢቢሲ፡ አንተን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ተከትሎ ነበር ወደ እስር የገባችሁት። ታስረህ በቆየህበት ቦታ ምን ተመለከትክ?
አሚር፡ ቤተሰብ ይንገላታል እንጂ ለአንድ ጋዜጠኛ ይህ እንደ አንድ እድል ነው፤ አገሩን ለማየት። ምን አይነት የፍትህ ስርአት እንዳለ ያየሁበት አጋጣሚ ነው። በርካቶች የዚህ ቋንቋተናጋሪ ናችሁ እየተባሉ ነበር በማንነታቸው የታጎሩት። ብዙዎች ይደበደቡ ነበር።
ፍርድ ቤትም አይቀርቡም፤ እንዲሁም ከታሰሩ በኋላ ነበር ወንጀል የሚፈለግላቸው። እንደውም መርማሪዎች ሰዎች ከታሰሩ በኋላ ምን አድርገህ ነው የመጣኸው እያሉ እንግልት ያደርሱ ነበር።
ባል ከነ ሚስቱ፣ ወንድማማቾች እንዲሁም እናት እና ልጅ ለወራት ታስረው ሲንገላቱ አይቻለሁ። ምግብ እንዲሁም የቤተሰብ ጥየቃ አስቸጋሪ ነበር። ባጠቃላይ አስከፊ ነገር አይቼ ነው የወጣሁት። ግዜው የኮሮና ነበር እና አንድ ክፍል ውስጥ ከ 40 በላይ ሰዎች ሆነን ነበር የታሰርነው። በርካቶች የሚታመሙም ነበሩ።
ነገር ግን ባለቤቴ፣ እናቴ እና ወንድሜ እንዲሁም ሌሎች ቤተሰቦቼ በጣም ተቸግረው ነበር። እኔን ለመጠየቅ ለሊት 7 ሰአት መጥተው ነበር ሰልፍ የሚይዙት። በዚህ አጋጣሚ ቤተሰቦቼን፣ ጓደኞቼን እንዲሁም የተለያዩ አለማቀፍ ተቐማት ላደረጉልኝ በጎ ጥረቶች ማመስገን እፈልጋለሁ።
ቢቢሲ፡ ያጋጠመህ እስር ከዚህ በኋላ የስራ ዘርፍህን እንድትቀይር አሳስቦህ ይሆን? በጋዜጠኝነት ስራህስ ትቀጥላለህ?
አሚር፡ ዋናው ጥያቄ ለህሊናዬ "ወንጀል ሰርቻለሁ ወይ" ለሚለው መልስ ማግኘት ነው። የጸጥታውን ስራ የሚሰሩ ሰዎች እንደተራ ሽፍታ ሰው አፍነው አቆዩ እንጂ እኔ በዳይ አይደለሁም። እንደውም ተበድያለሁ ብዬ ነው የማስበው። ለህሊናዬም ለሕግም ልክ ነው ብዬ ያሰብኩትን ነው የሰራሁት፤ ወደፊትም መስራቴን እቀጥላለሁ።
ቤተሰብ በጥየቃ እና መሰል ጉዳዮች ይንገላታል እንጂ እኔ ያን ያህል ትልቅ ነገር እንደደረሰብኝ አልቆጥረውም። እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገር ላይ ጋዜጠኝነት በርካታ ፈተናዎች ያሉበት ስራ ነው። ከዚህ የከፋ ነገርም ይገጥማል። ጋዜጠኝነቱን ወዶ ፈተናውን ጠልቶ አይሆንም። ሌሎች ብዙ ሰዎች ካሳለፉት አንጻር እኔ ያሳለፍኩት ቀላል ነው።
እነዚህን ፈተናዎች አምኖ መቀበል የማይፈልግ ሰው ጋዜጠኝነትን ባይሞክረው ይሻላል። ስለዚህ ይህንን ስራው ላይ ሊገጥም እንደሚችል አንድ ችግር [Occupational Hazard] እንጂ ስራውን ሊያስተወኝ የሚችል ነገር አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም።