ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው የፀረ ስደተኞች ቡድን መሪ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ታሰረ
በደቡብ አፍሪካ ፀረ ስደተኞች ቡድን መሪ የሆነው ግለሰብ በአገሪቱ የንግድ ከተማ ጆሃንስበርግ ውስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተነገረ።
ንህላንህላ ለክስ ድላሚኒ የተባለው የ33 ዓመቱ ወጣት ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በመጡ ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ቡድን መሪ ሲሆን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለበት ምክንያት እስካሁን ግልጽ አልሆነም።
ይህ ግለሰብ ከወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት ወቅት የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ከማግኘቱም በተጨማሪ በቦሌ አየር ማረፊያ አቀባበል ተደርጎለት ነበር።
መገናኛ ብዙኃኑ ድላሚኒ የአፍሪካ አንድነት አቀንቃኝ፣ የደቡብ አፍሪካ ማኅበረሰብ መሪ መሆኑን እና በወቅቱ ትኩረትን አግኝቶ የነበረውን #NoMore እንቅስቃሴ ለመደገፍ አዲስ አበባ መግባቱ ተዘግቧል።
ግለሰቡ የሚመራው ቡድን 'ኦፕሬሽን ዱዱላ' የተባለ ሲሆን ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች ከደቡብ አፍሪካ እንዲባረሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚያደርግ መጤ ጠል ስብስብ ነው።
ግለሰቡ በፖሊስ ተይዞ ጆሃንስበርግ ውስጥ ወደ ሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ ሲገባ ለጋዜጠኞች "ሕጋዊ ሂደት እንዲከናወን ፈቃደኛ ነኝ" ብሏል።
ድላሚኒ ጨምሮም የቡድኑ ተከታዮች በእሱ መታሰር ምክንያት ምንም አይነት የኃይል እርምጃ እንዳይወስዱ ጠይቋል።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ የቡድኑን ሌሎች መሪዎች ጠቅሶ እንደዘገበው ድላሚኒ ዛሬ አርብ ጠዋት ፍርድ ቤት ይቀርባል ብለው እየጠበቁ ነበር።
ይህ ፀረ ስደተኛ የሆነው ቡድን ችላ ተብለናል ብለው በሚያስቡ የደቡብ አፍሪካ ማኅበረሰቦች ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑ ይረነገራል።
ነገር ግን ይህ ቡድን የሚያካሂደው በውጭ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ቅስቀሳ በአገሪቱ ሌላ ዙር መጤ ጠል ጥቃቶችን እንዳይቀሰቅስ ስጋት ፈጥሯል።
ቢቢሲ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማናገር ባለፉት ቀናት በሰራቸው ዘገባዎች ይህ ቡድን የሚያካሂደው ቅስቀሳ ለደኅንነታቸው አስጊ ሁኔታን እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ኦፕሬሽን ዱዱላምንድን ነው?
የኦፕሬሸን ዱዱላ መቀመጫ በጆሃንስበርግ ሶፔቴ ነው።
በ33 ዓመቱ ንህላንህላ ለክስ ድላሚኒ የተመሰረተ ሲሆን የበለጠ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የሶዌቶ ነዋሪዎች ስደተኞችን "ጠራርገን እናስወጣቸው" የሚል ዘመቻ በጀመሩበት ወቅት ነበር።
ይህ ዘመቻ ትኩረት አድርጎ የነበረው የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎችን እና በሕገወጥ የመንግሥት ንብረቶችን ይዘዋል ባሏቸው ግለሰቦች ላይ ነበር።
ነገር ግን በአሌክሳንድራ ብቻ የቡድኑ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ እየሰፋ መጥቷል።
የዚህ ቡድን አባላት አሁን በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ በውጪ አገራት ዜጎች የተያዙ የንግድ ድርጅቶች ተዘግተው አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ይፈልጋሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አነስተኛ ንግዶች ደቡብ አፍሪካውያንን ብቻ ቀጥረው እንዲያሰሩ ፍላጎት አላቸው።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የዚህ ሃሳብ አቀንቃኞች በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ደቡብ አፍሪካውያንን ገሸሽ አድርገው በዝቅተኛ ዋጋ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን ይቀጥራሉ ብለው ስለሚያምኑ ነው።
ባለስልጣናት እንደዚህ አይነት አዝማሚያዎች ቢኖሩም ይህ ግን የተስፋፋ አለመሆኑን ይናገራሉ።
የቡድኑ አባለት መጤ ጠል አይደለንም ሲሉ ይናገራሉ። አክለውም የደቡብ አፍሪካውያን የዕለት ተዕለት ኑሮ ከአደጋ እየተከላከሉ መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚያም ወደ ኤኤንሲ፣ ገዢው ፓርቲ፣ ጣታቸውን በመቀሰር ይህንን ማድረግ ተስኖታል ሲሉ ይወነጅሉታል።
አባለቱ አክለውም ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ንክኪ እንደሌላቸው ይገልጻሉ።