ዓለምን ያነቃነቀው ከ45 ዓመታት በፊት የተለቀቀው የቦብ ማርሌ 'ኤክሶደስ' አልበም ሲታወስ

የቦብ ማርሌ 'ኤክሶደስ' የተሰኘው የሙዚቃ አልበም የተለቀቀው ከ45 ዓመታት በፊት ነበር።

በቅርቡ ደግሞ ስለ ሬጌው ንጉሥ የሙዚቃ ሕይወት የሚያወሳ አውደ ርዕይ ለንደን ውስጥ ይካሄዳል።

ምንም እንኳን ይህ አልበም በአውሮፓውያኑ 1977 ቢሆንም የወጣው ዓለም አቀፍ ተወዳጅነቱ፣ ተቀባይነቱ እንዳለ ነው።

ለሙዚቃው ዓለም አዲስ የሆኑ አልያም ለሙዚቃ እምብዛም ፍቅር የሌላቸው የዘመናችን ወጣቶችም ጭምር ቦብ ማርሌንና ይህንን አልበም በደንብ አድርገው ያውቁታል። ይህ በሁሉም የዓለማችን ክፍል እውነት ነው።

ኤክሶደስ የተጻፈበት መንፈስ የሰምና ወርቅ ዓይነት ነው።

በብሉይ ኪዳን ሙሴ ሕዝቡን ወደ ሰላማዊ ቦታ ያመጣበትን አጋጣሚ እና ቦብ ማርሌ የሚከተለው የራስታፋሪያን እምነት አስተምህሮት ጋር የሚቆራኝ አልበም ነው ኤክሶደስ።

ኤክሶደስ ትርጓሜው ስደት እንደማለት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ጃማይካ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ከባድ ውጥንቅጥ ውስጥ እያለች ቦብ ወደ ለንደን የተጓዘበትን አጋጣሚ እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 1976 ላይ እሱና ባለቤቱ ሪታ ማርሌ ላይ የግድያ ሙከራ ተደርጎ የደረሰበትን አካላዊ ጉዳት ለመግለጽ ነው ይህንን አልበም የሠራው የሚሉም አሉ።

በዩኬዋ ዋና ከተማ ለንደን ለአንድ ዓመት ያህል የቆየ ሲሆን ይህ ኤክሶደስ የተባለው አልበምም የተጠነሰሰው እዛው ለንደን ውስጥ ነው።

ቦብ ማርሌ ጃማይካ ውስጥ የተደረገበትን የግድያ ሙከራ አምልጦ ለንደን ከገባ በኋላ ነው ይህንን ዓለምን ከዳር እስከ ዳር ያነጋገረ አልበም የጻፈው።

"ይህ አልበም የፖለቲካ እና ባህልን ጥምረት ያሳየ ነው"

ኤክሶደስ በታይም መጽሔት በ20ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ በጣም አስፈላጊው አልበም ተብሎ ተመርጧል።

ይህንን ትልቅ ማዕረግ ለዚህ አልበም በሰጠበት ወቅት መጽሔቱ እንዲህ ብሎ ነበር፦

"ይህ አልበም የፖለቲካ እና ባህልን ጥምረት ያሳየ ነው። በሦስተኛው ዓለም አገራት ላይ ተመሥርቶ ይህንን እውነታ ለዓለም አሳይቷል።"

ይህ አልበም ዋን ላቭ የተሰኘውን ሙዚቃ እንዲሁም መንፈስን የሚያነቃቃው ኤክሶደስን ማካተቱ በራሱ ልዩ ያደርገዋል።

ታዲያ በለንደን ይህን ታላቅ ሙዚቀኛና ኤክሶድ የተሰኘውን አልበሙን ለመዘከር ሳቺ ጋለሪ የተሰኘ ተቋም አንድ ትልቅ አውደ ርዕይ አዘጋጅቷል።

ሁሉም የአውደ ርዕዩ ክፍሎች ቦብ ማርሌን በደንብ የሚገልጹና ባለቤቱ ሪታ ማርሌ የነበራትን ተጽዕኖ የሚያሳዩ ናቸው።

ታዲያ ይህ አውደ ርዕይ በለንደን ብቻ የሚቆም አይደለም።

በካናዳ ቶሮንቶ አድርጎ ቫንኩቨርን ነክቶ ወደ አሜሪካዎቹ ሎስ አንጀሊስ፣ ቺካጎ፣ ኒው ዮርክና ማያሚ ያቀናል።

ከእነዚህ ከተሞች ቀጥሎ ደግሞ አምስተርዳም፣ ሴውል፣ ቴል አቪቭ፣ ቶኪዮ እና ኪንግሰተን ይካሄዳል። የቦብ ተጽዕኖ በመላው ዓለም ይሰማል፣ ይታያል።

"ቦብ ስላለፈባቸው መከራዎች የሚገልጹ ብሶትና ለቅሶዎች ናቸው"

"ኤክሶደስ በንዴት የተሞላ አልበም ኤይደለም፤ ቦብ ስላለፈባቸው መከራዎች የሚገልጹ ብሶትና ለቅሶዎች ናቸው" ትላች የቦብ ልጅ ሴድላ ማርሌ።

ለኤክሶደስ አልበም 40ኛ ዓመት መታሰቢያ አልበሙ በልጆቹና በልጅ ልጆቹ በድጋሚ ተሠርቷል።

የሴድላ ወንድም ዚጊ ማርሌ በድጋሚ ድንቅ አድርጎ ያቀናበረው ይህ አልበም ለሰሚ ጆሮ አስደሳች ነው።

ከፖለቲካዊ እስከ መንፈሳዊ መልዕክቶች፣ ከመንግሥት እስከ ተራው ሕዝብ ድረስ የሚሠሩ በደሎችንና ጭቆናዎችን እንዲሁም ፍቅርና የልብ መሰበርንም አካትቶ የያዘ ታላቅ አልበም ነው።

ሙቭመንት ኦፍ ጃህ፣ ጃሚንግ፣ ዌይቲንግ ኢን ቬይን (ይህ ሙዚቃ ለወዳጁ ሲንዲ ብሬክስፒር የጻፈው እንደሆነ ይነገራል) የሚሰኙትን ሙዚቃዎች ሰምቶ በሐዘን፣ በአመጽ፣ በፍቅር፣ በሰላምና ተስፋ ስሜቶች ውስጥ አለመግባት ከባድ ነው።

"መልዕክቱ አሁንም ድረስ በጣም ጠቃሚ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ ቦብ ያሰማቸው ብሶቶችና ተቃውሞዎች አሁንም ድረስ አሉ። እኔም ሳረጅ ልጆቼም ሲያረጁ በተመሳሳይ ፍቅርና ፍላጎት ነው የምንሰማው። በ1970ዎቹ አካባቢ ጃማይካ ከባድ ነውጥ ውስጥ ነበረች። በዓለማችን የትኛውም ክፍል ሄዶ አልበሙን መሥራት ይችል ነበር፤ ነገር ግን ለንደንን መረጠ። ኤክሶደስ የቁጣ አልበም አይደለም'' ትላለች ልጁ።

"ኤክሶደስ የፈጠራ እርምጃ ነበር"

ኤክሶደስ ሲሠራ ከጅምሩ ከነቦብ ጋር የነበረችው የሙዚቃ ጸሐፊዋ ቪቪየን ጎልድማን ይህ አስገራሚ አልበም እንዴት እንደተጻፈ የሚያወሳ 'ዘ ቡክ ኦፍ ኤክሶደስ' የተሰኘ መጽሐፍ ጽፋለች።

"ኤክሶደስ የፈጠራ እርምጃ ነበር። ከተለመደው የሙዚቃ አሠራር ለየት ያለ ግን ምን እንደሆነ የማይታወቅ ነገር መፈለግ ነበር ይህ አልበም። የሬጌን መሠረት ሳይለቅ ለሌሎችም አድማጮች የሚደርስ ነው" ስትል ጽፋለች።

ሴት ልጁ ደግሞ "ቦብ ወደ ለንደን ሲሄድ በጣም ተናድጄበት ነበር። ለምን እኛን ጃማይካ ጥሎን ወደ ለንደን ሄደ ብዬ ተናድጄበት ነበር። ነገር ግን ለንደን ውስጥ አንድ በጣም የተለየ ነገር ነው የሠራው። የሆነች አንዲት ክፍል ውስጥ ቁጭ ብሎ ሰዎች እየገቡ እየወጡ ሲመለከት። ከነሱ ጋር በጣም ጥሩ ጊዜ ሲያሳልፍ፣ ሐዘኑንም መርሳት ሲያቅተው ለምን አዲስ ዓይነት ሙዚቃ አልሞክርም ያለ ይመስለኛል። አዲስ ነገር ለመሞከር ደግሞ አልፈራም" ስትል የአልበሙን ቀለም ታብራራለች።

በለንደን ነዋሪ የሆኑትና ከቦብ ጋር ቅርብ ቁርኝት የነበራቸው ዶን ሌትስ ስለ ቦብ ተናግረው አይጠግቡም።

"ለንደን ውስጥ ከኔ ቤት ትንሽ ራቅ ብሎ ነበር የሚኖረው። በወቅቱ ለንደን ውስጥ ተወዳጅ ስለሆነው የፓንክ ሙዚቃ ስልት ተከራክረን ነበር። መጀመሪያ ላይ ይህንን ስልት በጣም አጣጥሎት ነበር። እኔ ግን እንደተሳሳተ እየነገርኩት ተከራክረናል። በመጨረሻም ግን ቦብ የፓንክ ሙዚቃ ስልት እየገባው መጣ" ሲሉ ያስታውሳሉ።