ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሩሲያ ኃይሎች በተያዘችው የዩክሬን የወደብ ከተማ የሚንገላቱ አፍሪካውያን ተማሪዎች
የዩክሬን የወደብ ከተማ ኬርሶን በሩሲያ ኃይሎች እጅ ከወደቀች ከሁለት ሳምንት በላይ ተቆጥሯል።
በዚች የወደብ ከተማ የሚኖሩ ወደ 100 የሚጠጉ አፍሪካውያን ተማሪዎች ከከተማዋ ለመውጣት እርዳታ እንዲደረግላቸው እየተማጸኑ ነው።
ለቀናት ያህል በዩኒቨርስቲ ውስጥ ምድር በታች በተገነቡ ማቆያዎች ነው የተጠለሉት።
እነዚህ ማቆያዎች እጅግ ቀዝቃዛ ናቸው። ማሞቂያ የላቸውም። መድኃኒትም በቅርብ ርቀት አይገኝም።
በዚች የዩክሬን ደቡባዊ ከተማ የሚገኙ ተማሪዎች እየተንገላቱ እንደሆነ ይናገራሉ። በአፋጣኝ ከከተማዋ እንዲወጡ እርዳታ እንዲደረግላቸውም ይጠይቃሉ።
አንድ ተማሪ ለቢቢሲ እንደገለጸው አሁንም ድረስ እጅግ የሚያስበረግግ የተኩስ ድምጽ ይሰማቸዋል።
የፈንጂ እና ወታደራዊ አውሮፕላኖች ድምጽም ይረብሻቸዋል።
ተማሪዎቹ የሚሰማቸው ድምጽ የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬንን ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ለመያዝ ከሚያደርጉት ውጊያ ሊሆን ይችላል።
የሩሲያን መስፋፋት የሚቃወሙ ሰዎች ላይ የሩሲያ ኃይሎች እየተኮሱ ነው።
የናይጄሪያ መንግሥት ሳይዘገይ ከዩክሬን እንዲያስወጣቸው ናይጄሪያውያን ተማሪዎች እየወተወቱ ይገኛሉ።
በዩክሬኗ የወደብ ከተማ ከሚገኙ የመጨረሻዎቹ አፍሪካውያን መካከል እንደሚገኙበት ተማሪዎቹ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ የማይጠቀስ አንድ ተማሪ ለቢቢሲ በስልክ "እባካችሁ ከዚህ አስወጡን ብለን እየለመንን ነው። ያለንበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው" ብሏል።
የናይጄሪያ መንግሥት ተማሪዎቹን ለማስወጣት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።
ተማሪዎቹ በሩሲያ በኩል እንዲወጡ ለማስቻል አውሮፕላኖች እየተዘጋጁ መሆኑን በሩሲያ የናይጄሪያ አምባሳደር ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።
ነገር ግን እስካሁን ድረስ ተማሪዎቹ አልወጡም።
በተጨማሪም ተማሪዎቹ ወደ ሩሲያ መሄድ ያሰጋቸዋል።
የካሜሩን፣ የጋና፣ የግብፅ፣ የቱኒዚያ እና የሞሮኮ ዜጎች የሆኑ ተማሪዎችም በዚያው ከተማ ይኖራሉ።
በሚማሩበት ዩኒቨርስቲ አሁን ጥቂት ምግብ ቢኖርም መደብሮች ውስጥ ሸቀጥ እያለቀ እንደሆነ ይናገራሉ።
ገበያ ላይ የቀረው ምግብ እየተሸጠ ያለው በእጥፍ ወይም በሦስት እጥፍ ዋጋ ነው።
አንዲት ተማሪ "ዩኒቨርስቲው አሁንም ድረስ ምግብ እያቀረበልን ስለሆነ በአንጻራዊነት የተሻለ ሁኔታ ውስጥ ነን" ብላለች።
ሌላ ተማሪ እንዳለው ደግሞ ከተማዋን የተቆጣጠሩት የሩሲያ ኃይሎች አትክልቶች፣ ሩዝ፣ ፓስታ እና ውሃ በመንግሥት ሕንጻዎችና በባቡር አቅራቢያ እያቀረቡላቸው ነው።
ነገር ግን ይህንን ምግብ መቀበል በዩክሬናውያን ዘንድ ከሩሲያ ጋር እንደማበር ስለሚቆጠር ያሰጋል።
"ዩክሬናውያን አገራቸውን ለመታደግ እየተዋደቁ እንዴት የሩሲያን እርዳታ እንቀበላለን? ይህንን ምግብ ተቀበሉ የሚለን ሰው ሞታችንን ነው የሚያፋጥነው" ብሏል ተማሪው።
ልብስ ለማጠብ ውሃ ቢገኝም የመጠጥ ውሃ ግን ተመናምኗል።
የእርዳታ ድርጅቶች ምግብ እና ውሃ እያደረሱ ቢሆንም እስከ መቼ እንደሚዘልቅ አይታወቅም።
የወደብ ከተማዋ በወረራው የመጀመሪያ ሳምንት በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ከገቡ የመጀመሪያዎቹ ከተሞች አንዷ ናት።
የወደብ ከተማዋን የሩሲያ ኃይሎች ከተቆጣጠሩበት ጊዜ አንስቶ የከተማዋ ነዋሪዎች ተቃውሞ እያካሄዱ ነው።
"ወደዚህ አገር የመጣነው ለትምህርት ነበር። አሁን ግን ጦርነት ውስጥ ወደቅን። ዩክሬናውያን እጅ እንደማይሰጡ ነግረውናል። ከተማቸውን እንዲሁም አገራቸውን በአጠቃላይ ማስመለስ ይፈልጋሉ" ብሏል አንድ ተማሪ።
ሩሲያውያን ወታደሮች ምግብ ወደ ከተማዋ እንዳይገባ እንደከለከሉም ተናግሯል።
የዩክሬን ኃይሎች ምግብ ወደ ከተማዋ ለማስገባት በሚል ወደ ውጊያ እንዳይገቡ ነው የሩሲያውያኑ አላማ።
አንዲት ተማሪ "በየቀኑ ቤተሰቦቼ ይደውላሉ። ግን አንዳችም መልካም ዜና ስለሌለኝ ስልኩን ማንሳት ያስፈራኛል። በቅርቡ ከዚህ የምንወጣ አይመስልም" ብላለች።
ጦርነቱ ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ እናቷ በየቀኑ እያለቀሰች እንደምትጸልይም አክላለች።
ተማሪዎቹ ከዩኒቨርስቲው መውጣት ያለባቸው በቡድን ብቻ እንደሆነ ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።
ከዩኒቨርስቲው ቅጥር ጊቢ ሲወጡ ክንዳቸው ላይ ነጭ ጨርቅ እንዲያስሩም ተመክረዋል። ተማሪዎቹ ለሩሲያ ኃይሎች ንጹሀን ዜጎች መሆናቸውን ለማሳወቅ ነው ነጭ ጨርቅ የሚያስሩት።
ከ'መስመር' የወጣ ሰው ካዩ እንዲተኩሱ የሩሲያ ኃይሎች ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው አንድ ተማሪ ገልጿል።
በዩክሬን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአፍሪካ እና ደቡብ እስያ ተማሪዎች ይኖሩ ነበር።
ከእነዚህ አብዛኞቹ ዩክሬንን ለቀው ሲወጡ፤ የተቀሩት ደግሞ በጎረቤት አገሮች ትምህርታቸውን ቀጥለዋል።
በዩክሬኗ የወደብ ከተማ ኬርሶን የሚገኙ ተማሪዎች ግን አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።
አንዳንዶቹ በድፍረት ታክሲ ተኮናትረው ከከተማዋ ለመውጣት ሞክረዋል።
አንድ ተማሪ "ከዚህ ከተማ ለመውጣት የሚሞክሩ ተማሪዎች ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ። አንዳንድ የሩሲያ ወታደሮች ተማሪዎቹ እንዲመለሱ በትህትና ይነግራሉ። አንዳንዶቹ ወታደሮች ግን በጭካኔ ይተኩሳሉ" ብላለች።