ዩኬ የኤምባሲ ሠራተኞቿን ከዩክሬን ስታስወጣ አሜሪካ ደግሞ ሠራተኞቿ እንዲወጡ አሳሰበች

በዩክሬን የአሜሪካ ኤምባሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዩክሬን የአሜሪካ ኤምባሲ

ከሩሲያ ጋር የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በዩክሬን የሚገኙ የኤምባሲ ሠራተኞቿን ማስወጣት መጀመሯ ተነገረ።

የዩኬ ባለሥልጣናት ምንም እንኳ በዲፕሎማቶቻቸው ላይ የተለየ የደኅንነት ስጋት ባይኖርባቸውም ኪዬቭ በሚገኘው ኤምባሲ የሚሰሩ ግማሽ ያክል ሠራተኞች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ይመለሳሉ ብለዋል።

ይህ የዩኬ መንግሥት ውሳኔ የተሰማው አሜሪካ በቀጠናው እየበረታ የመጣውን ውጥረት ተከትሎ በዩክሬን የሚገኘው ኤምባሲዋ ሠራተኞች አገሪቱን ለቀው በአስቸኳይ እንዲወጡ ማሳሰቢያ መስጠቷ ከተሰማ በኋላ ነው።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኛ ያልሆኑ ሰዎችም ከዩክሬን እንዲወጡ ከማሳሰቡም በላይ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ሰዎችም እንዲወጡ መክሯል።

መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ እንደሆነ የሚያሳይ በቂ መረጃ አለ ብሏል።

ሞስኮ በበኩሏ ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ነው የሚባለው ወሬ ሐሰት ነው ስትል ታስተባብላለች።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አክሎም አሜሪካውያን ወደ ዩክሬንና ሩሲያ ባይጓዙ ይመረጣል ሲል ያስጠነቀቀ ሲሆን "አሜሪካውያን ላይ ትንኮሳ ሊደርስ ይችላል" ብሏል።

የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣን ኤኤፍፒ ለተሰኘው የዜና ወኪል እንደተናገሩት ዩክሬን የሚገኘው ኤምባሲ አሁንም ክፍት ቢሆንም በየትኛውም ሰዓት ወረራ ሊኖር እንደሚችል ከዋይት ሐውስ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል ብለዋል።

ባለሥልጣኑ አክለው "መንግሥት አንዳች ነገር ቢከሰት ዜጎቹን ካሉበት ፈልጎ የሚያወጣበት አቋም ላይ አይደለም" ብለዋል።

ይህ የአሜሪካ ድርጊት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በየትኛውም አካባቢ የአሜሪካውያን ዲፕሎማቶች ሕይወት አደጋ ላይ ነው ብሎ ሲያስብ የሚፈፅመው ነው።

ነገር ግን ባለፉት 24 ሰዓታት ይህንን መግለጫ ሊያሰጥ የሚችል ምንም አዲስ ነገር እንዳልተከሰተ እየተነገረ ነው።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን [ኔቶ] ሠራዊት አዛዥ፤ ሩሲያ በግምት 100 ሺህ ወታደሮቿን ድንበር አካባቢ ካሰፈረች በኋላ አውሮፓ ውስጥ አዲስ ግጭት አይቀሬ እንደሆነ ተናግረዋል።

ባለፈው ቅዳሜ 90 ቶን የሚመዝን የጦር መሣሪያን ጨምሮ በርካታ እርዳታ ከአሜሪካ ተነስቶ ዩክሬን ገብቷል።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እንደሚሉት መንግሥታቸው የዩክሬንን ሠራዊት ከማገዝ ጀምሮ ቭላድሚር ፑቲን ስሌታቸውን እንዲያጤኑ የሚያስችላቸው የተለያዩ ተግባራትን እየከወነ እንደሆነ ገልጠዋል።

ሩሲያ፤ በፈረንጆቹ 2014 ዩክሬን ለሞስኮ የሚወግነውን መንግሥት ከሥልጣን ማንሳቷን ተከትሎ የዩክሬን አካል የነበረችውን ክሬሚያን ወራ መውሰዷ ይታወሳል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዩክሬን ወታደራዊ ኃይል በሩሲያ ከሚደገፉ አማፂያን ጋር በየጊዜው የሚፋለም ሲሆን ዶንባስ በተሰኘው ሥፍራ እስካሁን 14 ሺህ ሰዎች በዚህ ግጭት ሳቢያ እንደሞቱ ይገመታል።

እሑድ ዕለት የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ፑቲን ለሞስኮ የሚያደላ መንግሥት ዩክሬን ውስጥ መመሥረት ፈልገዋል ሲል ወቅሷል።

ሩሲያ ዩክሬንን የምትወር ከሆነ ከባድ እርምጃ እንደሚጠብቃት የዩናይት ኪንግደም ሚኒስትሮች አስጠንቅቀዋል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናትም እንዲሁ ሩሲያ የዩክሬን መንግሥትን ፈንቅላ ለሞስኮ የሚወግን መንግሥት ትሾማለች የሚል ስጋት አላቸው።