የቤንያሚን ኔታንያሁ የሙስና ክስ በቅጣት ድርድር ሊቋጭ እንደሚችል ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሙስና የተከሰሱት የእስራኤል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የፍርድ ሂደቱን ለማስቆም የቅጣት ድርድር እያደረጉ እንደሆነ ቢቢሲ ከቅርብ ምንጭ ተረድቷል።
በቅጣት ድርድሩ መሰረት የ72 አመቱ ቤንያሚን ኔታንያሁ በተወሰነ ደረጃ ጥፋተኝነታቸውን ማመን የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህም ከሆነ ወንጀላቸው ተቀንሶ በእስር ፋንታ በማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሳተፉ ሊያደርግ የሚያስችል ነው።
ኔታንያሁ በበኩላቸው ጥፋተነኝነታቸውን ካመኑ ከፖለቲካው ዓለም እንዲገለሉ የሚያስገድደውን ይህንን የቅጣት ድርድር ለመቀበል መቃወማቸውን በተመለከተ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
እስራኤልን ለረዥም ዘመን ያስተዳደሯት ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈው አመት ከተካሄደው ምርጫ በኋላ ራሳቸውን ከፖለቲካው ገለል አድርገዋል።
በእስራኤል ፓርላማ ውስጥ ትልቁ ፓርቲ የሆነው የቀኝ ክንፉ ሊኩድ መሪ ሲሆኑ አገራቸውንም ለ15 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።
ባለፉት አምስት አመታት የስልጣን ዘመናቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች ፖሊስ ምርመራ የከፈተባቸው ሲሆን የፍርድ ሂደቱም በአውሮፓውያኑ 2020 ተጀምሯል።
በጉቦ፣ በማጭበርበር እና እምነት በማጉደል የተከሰሱት ቤንያሚን ኔታንያሁ እሳቸው ግን ክሶቹ ፖለቲካዊ አላማ አላቸው በማለት ውድቅ አድርገዋቸዋል።
ኔታንያሁ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ አቪቻይ ማንደልብሊት ጋር በቅጣት ድርድር ላይ መወያየታቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች በቅርብ ቀናት ውስጥ ከእስራኤል ሚዲያዎች ተስምተዋል።
ለቅጣት ድርድሩ ጋር ቅርበት ያላቸውና ስማቸው ያልተጠቀሰ ምንጭ እሁድ እለት የቅጣት ድርድሩ መካሄዱን አረጋግጠዋል ሲሉ የዜና ወኪሎች ዘግበዋል።
የእስራኤሉ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ኔታንያሁ በተወሰነ መልኩ የጥፋተኝነት ደረጃን መቀበላቸውን ቤተሰቦቻቸው ቢቃወሙም ጠበቆቻቸው ውይይቱን እንዲቀጥሉ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ክስ ከሀብታም ወዳጃቸው ሻምፓኝ፣ ሲጋራና ሌሎችም ውድ ስጦታዎች በጉቦ ተቀብለዋል የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የዜና ሽፋን ለማግኘት ከጋዜጣ አሳታሚ ጋር ተዋውለዋል የሚል ነው።
ከሁሉም ክሶች ከባዱ የተባለው የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ለዜና ሽፋን ሲሉ አውራ የቴሌኮም ድርጅትን የሚጠቅም ሕግ አስተዋውቀዋል የሚለው ነው።
በወቅቱ ሕጉ በባለሙያዎች የተደገፈ እንደሆነ የገለጹት ኔታንያሁ ይህ ክስ እስከ አስር ዓመት የሚሆን እስር እንዲሁም የገንዘብ ቅጣት ያስቀጣቸዋል ተብሎ ነበር።
እኚሁ ምንጭ እንደተናገሩት ክሶቻቸው እንዲቋረጡ ጥፋተኝነታቸውን እንዲያምኑና "የሞራል ውድቀት" የተባለውን ክስ እንዲቀበሉ ተጠይቀዋል። በዚህም መሰረት ለሰባት ዓመታት በፖለቲካው የሚታገዱ ሲሆን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን እየተቃወሙ ነው ተብሏል።
በፖለቲካዊ መሰረታቸው ጠንካራ ድጋፍ ያላቸው ኔታንያሁ አሁን ያለውን ጥምር መንግሥት ተቃውመው በቅርቡም ወደ ስልጣን የመመለስ አላማ እንዳላቸው ተናግረዋል።












