የቀድሞው የማሊ ፕሬዝደንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የቀድሞው የማሊ ፕሬዝደንት ኢብራሂም ቦባክር ኬይታ በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ቤተሰቦቻቸውና የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቻቸው አስታወቁ።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከሁለት ዓመት በፊት ቀለል ያለ ስትሮክ አጋጥሟቸው የነበረ ሲሆን ለሞታቸው ምክንያት የሆነው ነገር ግን ግልጽ አልተደረገም።

ኢብራሂም ቦባክር ኬይታ ትናንት በማሊ መዲና ባማኮ በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ህይወታቸው ማለፉን የቤተስብ አባል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ኬይታ አገሪቱን እስከ አውሮፓውያኑ 2020 ድረስ ለሰባት ዓመታት መርተዋል። ባሳለፍነው ዓመት ግን የጂሃዲስቶችን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ባለማቻለቸው የቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣናቸው መነሳታቸው ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ እና ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶች የቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ ተቃውሞ እንዲበረታ ያደረጉ ምክንያቶች ነበሩ።

ኢብራሂም ቦባክር ኬይታ ላለፉት 3 አስርት ዓመታት በፖለቲካው የቆዩ ሲሆን፤ እአአ ከ1994 እስከ 2000 ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።

ከመንግሥት ሰራተኛ ቤተሰቦች የተገኙት ኢብራሂም ኬይታ፤ ውልደታቸው በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በምትገኘው ኮቲሊያ ከተማ ነው። ኬይታ ስነ ጽሁፍ፣ ታሪክ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አጥነተዋል።

ፈረንሳይ ውስጥ ለአስርት ዓመታት የኖሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት በአንድ ወቅት እዛው ፈረንሳይ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፓሪስ ውስጥ በአስተማሪነት አገልግለዋል። በተጨማሪም የአውሮፓ እድገት ፈንድ ውስጥ በአማካሪነት ሰርተዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ደግ፣ ቁጡ እና ጠንቃቃ መሪ እንደነበሩ ባልደረቦቻቸው ይመሰክሩላቸዋል።

ማሊ ነጻነቷን ካገኘችበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ የደህንነት እና ፖለቲካዊ ቀውሶች ያጋጥሟት የነበረ ሲሆን 2012 ላይ ደግሞ ጂሃዳዊ እንቅስቃሴዎች ስጋት ፈጥረው ቆይተዋል።

2013 ላይ ደግሞ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንደሚያመጡ ቃል በመግባት ለፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩ ሲሆን በምርጫውም በከፍተኛ ድምጽ አሸንፈዋል።

ነገር ግን አስተዳደራቸው ቃል በገባው መሰረት ማሊን ሰላማዊና የተረጋጋች ማድረግ ተስኖት ቆይቷል። ይህንን ተከትሎም ፕሬዝዳንቱ 2020 ላይ በወታደሮቻቸው በተፈጸመ መፈንቅለ መንግሥት ከስልጣናቸው ተባረዋል።

ከሳምንታት በኋላ አነስተኛ ስትሮክ አጋጥጥሟቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በወቅቱም ህክምና ለማድረግ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አቅንተዋል።

ከስልጣናቸው ከተባረሩ በኋላ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በዋና ከተማዋ ባማኮ ይኖሩ ነበር። ስለ እንቅስቃሴያቸውም ብዙ እንዲታወቅ አይፈልጉም ነበር። ነገር ግን ወንድ ልጆቻቸው ወደሚኖሩባት አይቮሪ ኮስት በተደጋጋሚ ይመላላሱ እንደነበር ተዘግቧል።

አሁን ላይ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ላይ ያለው የማሊ ወታደራዊ መንግሥት በሚቀጥለው ወር ሊካሄድ ታቅዶ የነበረውን ምርጫ ለሶስት ዓመታት እንዲራዘም አድርጓል።

ይህንን ተከትሎ የአውሮፓ ሕብረት እና ጎረቤት አገራትም ጭምር ማዕቀቦችን እንዲጥሉ ሆኗል።