በማይ አይኒ በተፈጸመ ጥቃት ሦስት ኤርትራውያን መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ገለጸ

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ሦስት ኤርትራውያን በማይ አይኒ የስደተኞች ጣቢያ በአየር ጥቃት መገደላቸውን አስታወቀ።

ከሦስቱ ኤርትራዊያን ስደተኞች መካከል ሁለቱ ሕፃናት መሆናቸውን ኮሚሽኑ በኦፊሴላዊ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በመግለጫው ላይ በጥቃቱ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ሰዎች መፅናናትን እመኛለሁ ብለዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም ድርጅታቸው ባለው መረጃ መሠረት አራት ተጨማሪ ሰዎች በጥቃቱ የተጎዱ ቢሆንም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አሳውቀዋል።

ግራንዲ፤ ስደተኞች የመሰል ጥቃቶች ሰለባ ሊሆኑ አይገባም ሲሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

ኃላፊው አክለው በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭት ተሳታፊ የሆኑ አካላት ስደተኞችን ጨምሮ የሰላማዊ ዜጎችን መብት እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት በድረ-ገፁ ባወጣው መግለጫ በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች 5.2 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ ይሻሉ ብሏል።

የመንግሥታቱ ድርጅት እንደሚለው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጦርነቱ ምክንያት ተገድለዋል፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል።

"በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ አስፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። አሁን ብቸኛው ወደ ክልሉ እርዳታ የሚገባበት መስመር ከሰመራ በአባላ ወደ መቀለ የሚወስደው ነው። ከታኅሣሥ 6 ወዲህ ወደ ትግራይ ክልል ምንም ዓይነት እርዳታ አልገባም" ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ሐሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የተራድኦ ሠራተኞች አሁንም በአፋርና አማራ ክልሎች እንዲሁም በምዕራብ ትግራይ ሰላማዊ ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው ማለታቸውን የተባበሩት መንግሥታት አመልክቷል።

"ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ያሉ ሰዎች አሉ። ምግብ፣ ውሃ፣ የንፅህና መገልገያና መጠለያ ያስፈልጋቸዋል" ሲሉ ስቴፋን ያክላሉ።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተዛምቶ የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች በተለያየ ደረጃ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግና የስደተኛ ሕግ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን የመብት ተቆርቋሪዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።