አንቶኒ ብሊንከን እና ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያና በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ተወያዩ

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በቅርቡ ኬንያን በጎበኙበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, State House Kenya

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በቅርቡ ኬንያን በጎበኙበት ወቅት

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታና በሌሎች የቀጠናው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተነገረ።

የኬንያው ፕሬዝዳንት እና የውጭ ጉዳይ ኃላፊው በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ያለውን ሁኔታ ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸው ተገልጿል።

ብሊንከን እና ኬንያታ በውይይታቸው ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት አንስተው መነጋገራቸውን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

በዚህ ውይይትም የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማስቆም አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ ሰብአዊ እርዳታ ያለገደብ እንዲቀርብ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የሚፈጸሙ ግፎች እንዲቆሙ እንዲሁም ጦርነቱ በድርድር መቋጫ እንዲያገኝ እንዲደረግ መስማማታቸውን መግለጫው ጠቅሷል።

ከአንድ ወር በፊት የህወሓት አማጺያን ወደ መሃል አገር ተቃርበው ጦርነቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ መንግሥት ባካሄዳቸው ተከታታይ ወታደራዊ ዘመቻዎች በርካታ የአማራና የአፋር ክልል ቦታዎችን መቆጣጠሩ ይታወሳል።

የህወሓት መሪዎችም ተዋጊዎቻቸውን ከሁለቱ ክልሎች በማስወጣት ወደ ትግራይ መመለሳቸውን በመግለጽ የሰላም ድርድር ጥያቄን በይፋ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ይፋ እንዳረገው ሠራዊቱ በህወሓት ተይዘው የነበሩ የአፋርና የአማራ ክልል ቦታዎችን ማስለቀቁን ተከትሎ ዘመቻውን ወደ ትግራይ ክልል እንደማይቀጥል አሳውቋል።

የአሜሪካ መንግሥት እና የተባበሩት መንግሥታትም በሁለቱም ወገኖች ግጭቱን ለመግታት የተወሰደውን እርምጃ እንደሚደግፉት ገልጸው ውይይት እንዲጀመር አበረታተዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን፤ ፕሬዝዳንት ኬንያታና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ጦርነቱን በሽምግልና ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት አሜሪካ በጥብቃ እንደምትደግፈው ገልጸዋል።

ጦርነቱ በተባባሰበት ጊዜ የአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይ የሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ እና መቀለ በመሄድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትና ከህወሓት መሪዎች ጋር የተነጋገሩ ቢሆንም ምን ምላሽ እንዳገኙ የተባለ ነገር የለም።

አንድ ዓመት ባስቆጠረው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ባይታወቅም በርካቶች ሕይወታቸውን እንዳጡ፣ ሚሊዮኖች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ እንደሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

ሶማሊያን በተመለከተ የአገሪቱ ፌደራላዊና ክልላዊ መሪዎች የምክር ቤትና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ነጻ በሆነ መንገድ በአስቸኳይ ማካሄዳቸው አስፈላጊ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው መናገራቸውን መግለጫው አመልክቷል።

ጨምረውም የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌን ፕሬዝዳንቱ ፋርማጆ ለማገድ መሞከራቸውን አሜሪካ እንደምትቃወመው በመግለጽ፤ ሁሉም ወገኖች ችግሮችን ከሚያባብሱ ተግባራትና ንግግሮች እንዲቆጠቡ ብሊንከን መጠየቃቸው ተገልጿል።

ሰኞ ዕለት ሥልጣንን ያላግባብ ተጠቅመዋል፣ የመንግሥት መሬትንም ይዘዋል በሚል የሚደረግባቸው ምርመራ እስኪጠናቀቅ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ከሥልጣናቸው አግደዋቸው ነበር።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬዝዳንቱን የእገዳ ውሳኔ "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ" በማለት እንደማይቀበሉትና በሥራቸው እንድሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ይህም በሁለቱ ባለሥልጣናት መካከል ያለው አለመግባባት ወደ ግጭት እንዳያመራ ሥጋትን ፈጥሯል።