ከሄሊኮፕተር አደጋ በኋላ ለ12 ሰዓታት በመዋኘት ሕይወታቸውን ያተረፉት ሚኒስትር

ከአደጋ በኋላ ለ12 ሰዓታት በመዋኘት ሕይወታቸውን ያተረፉት ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, PRESIDENT ANDRY RAJOELINA/ TWITTER

አንድ የማደጋስካር ሚኒስትር የሚጓዙበት ሄሊኮፕተር ባሕር ውስጥ መከስከሱን ተከትሎ ለ12 ሰዓታት በመዋኘት ራሳቸውን መታደጋቸውን ገልጸዋል።

''መሞቻዬ አልደረሰም'' ሲሉ ተደምጠዋል የፖሊስ ሚኒስትሩ ሰርጌ ጌል የሕሙማን ማረፊያ አልጋ ላይ ጋደም ብለው ትንፋሽ ለመሰብሰብ እየሞከሩ።

ሄሊኮፕተር ውስጥ ከሚኒስትሩ ጋር ሲጓዙ የነበሩ ሌሎች ሁለት ኃላፊዎችም ከአደጋው ተርፈዋል።

የመንግሥት ኃላፊዎቹ ትናንት ማክሰኞ ዕለት በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ አካባቢ የሰጠመች የመንገደኞች መርከብ አደጋን ተከትሎ ነው ወደ ስፍራው ያቀኑት።

አሁን ላይ ቢያንስ 39 ሰዎች በአደጋው ሕይወታቸው ማለፉ የተገለጸ ሲሆን የአደጋው መንስኤ እስካሁን ድረስ አልታወቀም።

የማደጋስካሩ ፕሬዝዳንት አንድሬይ ራሆሊና በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት በአደጋው ምክንያት ዜጎቻቸው በመሞታቸው በጣም ማዘናቸውን በመግለጽ በሕይወት ለተረፉት የመንግሥት ኃላፊዎች ደግሞ እንኳን ተረፋችሁ ብለዋል።

ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ አደጋው በትክከል በምን ምክንያት እንደደረሰ ያልታወቀ ቢሆንም ከሄሊኮፕተር አደጋው የተረፉት የፖሊስ ሚኒስቴር ግን ከምሽቱ 1፡30 አካባቢ ጀምረው በመዋኘት ጠዋት 1፡30 ላይ ማሃምቦ የምትባል ከተማ ደርሰዋል።

ሚኒስትሩ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደሰባቸው የገለጹ ሲሆን ትንሽ ብርዱ ግን አስቸግሯቸው እንደነበር አልሸሸጉም።

''ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼ እንዲሁም የመንግሥት አካላት በሕይወት መኖሬን እንዲያውቁ ይህንን መልዕክት አስተላልፉልኝ'' ብለዋል ሚኒስቴሩ ማሃምቦ ውስጥ ለተሰበሰቡ መገናኛ ብዙኃን።

የፖሊስ ኃላፊው ዛፍሳምባትራ ራቮይ በበኩላቸው ሚኒስትሩ ለ12 ሰዓታት በመዋኘት ለመትረፍ የቻሉት አንደኛውን የሄሊኮፕተር መቀመጫ እንደ መንሳፈፊያ በመጠቀም መሆኑን ገልጸዋል።

''ስፖርት ሲሠራ በጣም ጥሩ ብቃት ያለው ሰው ነበር፤ ሚኒስትር ከሆነም በኋላ በዚሁ ነው የቀጠለው። ልክ እንደ 30 ዓመት ሰው ነው ሁኔታው፤ በጣም የሚያስገርም ሰው ነው'' ብለዋል ኃላፊው።

ሚኒስትሩ በፖሊስ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለሦስት አስርት ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን ባለፈው ነሐሴ ላይ ነበር የፖሊስ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት።