ምዕራባውያን በሩሲያ የመወረር ስጋት ውስጥ ናት ላሏት ዩክሬን ድጋፋቸውን ገለጹ

የምዕራቡ ዓለም ኃያላን መንግሥታት ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የገባችበትን ፍጥጫ ረገብ እንድታደርገው ጥሪ አቀረቡ።

አገራቱ ይህንን ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ሊያካሂዱት ካሰቡት የቪዲዮ ስብሰባ ቀደም ብሎ ነው።

ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ነው በሚል ስጋት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣልያን ጋር የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ተስማምተዋል።

ሞስኮ ግን በዩክሬን ላይ ምንም አይነት ጥቃት የመፈጸም እቅድ የለኝም ብላለች።

በሌላ በኩል ሩሲያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ምሥራቃዊ ድንበር ያስጠጋች ሲሆን የሩሲያ ታንኮች ወደ ድንበሯ በመጠጋት ቦታ መያዛቸውን ዩክሬን አስታውቃለች።

የሁለቱ መሪዎች ውይይት ከመካሄዱ በፊት ዋሽንግተን ከወታደራዊ አማራጭ ይልቅ ሩሲያ ላይ ጠንከር ያለ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ እንደ አማራጭ አቅርባለች።

ከሰሞኑ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሩሲያ በዩክሬን ላይ "መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመፈጸም" እቅድ እንዳወጣች የሚያሳይ ማስረጃ አገራቸው እንዳገኘች ገልጸዋል።

ነገር ግን ፕሬዚዳንት ፑቲን ዩክሬንን ለመውረር የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ግልጽ አይደለም ሲሉም አክለዋል።

ሩሲያ ግን አሁንም የማጥቃትም ሆነ የመውረር ሃሳብን ውድቅ አድርጋ ዩክሬን ሠራዊቷን በከፍተኛ ሁኔታ እያጠናከረች ነው ስትል ከሳታለች።

ሰኞ ምሽት በተደረገ የኮንፈረንስ ጥሪ አምስት የምዕራቡ ዓለም አገራት የሩሲያ ምጣኔ ሃብት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ መስማማተቸውን ዋይት ሐውስ አስታውቋል።

ሊወሰዱ ከሚችሉት እርምጃዎች መካከል የሩሲያን ሩብል ወደ ውጭ አገራት ገንዘቦች የሚቀይሩ ባንኮች ላይ ገደብ ማስቀመጥ አልያም ሩሲያን ከዓለም አቀፉ የስዊፍት ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ማስወገድ ይጠቀሳሉ።

በአውሮፓውያኑ 2014 ሩሲያ የክሪሚያን ግዛት ከዩክሬን ከወሰደች በኋላ ከፍተኛ የጦር መሳሪያና ወታደር በጋራ ድንበሩ ላይ ስታሰማራ የመጀመሪያው ነው።

በአሁኑ ወቅት ያለው የሩስያ ጦር እንቅስቃሴ በሩሲያ እና በአሜሪካ መካከል ቀደም ሲል ሻክሮ የነበረውን ግንኙነት የበለጠ ውጥረት እንዲነግስበት አድርጎታል።

የክሌምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ሩሲያ ወረራ ልትፈጽም ነው የሚለውን ውንጀላ አስቂኝና መሰረተ ቢስ ነው ሲሉ ተችተውታል።

እስከ 90 ሺህ የሚደርሱ የሩሲያ ወታደሮች ወደ ዩክሬን ድንበር ተጠግተው እንደሚኙ የተገለጸ ሲሆን በዩክሬን ድንበር በስተምሥራቅ በኩልም ወታደሮች መሰባሰብ ጀምረዋል ተብሏል።

የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትር ኦሌክሲይ ሬዝኒኮቭ የደኅንነት ዘገባዎችን በመጥቀስ ሩሲያ በጥር ወር መጨረሻ ወታደራዊ ጥቃትን ልትፈፅም እንደምትችል ተናግረዋል።

በሩሲያ የሚደገፉት ኃይሎች ስፋት ያለው የዩክሬንን ምሥራቃዊ ግዛት መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ላለፉት ሰባት ዓመታት በነበሩ ግጭቶች ምክንያት ከ14 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።