ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምጥ ላይ የነበሩት የኒውዚላንዷ የፓርላማ አባል ሳይክላቸውን ነድተው ሆስፒታል ደርሰው ወለዱ
ባሳለፍነው እሁድ የኒውዚላድ ተመራጭ እና ብስክሌትን ከመኪና ይልቅ የመጠቀም ቀንደኛ አቀንቃኝ የሆኑት ጁሊ አኔ ጌንቴር ሳይክላቸውን እያሽከረከሩ ሆስፒታል ከደረሱ ከአንድ ሰአት በኋላ ልጃቸውን ተገላገሉ።
ፖለቲከኛዋ ሳይክላቸውን እያሽከረከሩ በነበረበት ወቅት ምጥ ላይ ነበሩ።
«ከልብ ለመናገር ከሆነ ልጄን ለመገላገል ሳይክሌን እየነዳሁ እሄዳለሁ የሚል እቅድ አልነበረኝም። ግን የሆነው እሱ ነው» ሲሉም በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። የአረንጓዴ ፓርቲ ቃል አቀባይ የሆኑት ጁሊ ከሶስት አመት በፊትም ተመሳሳይ ጉዞ አድርገዋል።
የ 41 ዓመቷ ፖለቲከኛ ከባለቤታቸው ጋር ወደ ሆስፒታል በሳይክል ለመሄድ ሲወስኑ ምጣቸው ያን ያህል ከባድ እንዳልነበረ ተናግረዋል።
ከባለቤታቸው ጋር በሆስፒታሉ የመኪና ማቆሚያ ሲደርሱም ምስሎችን በመውሰድ በማህበራዊ መገናኛዎቻቸው አጋርተዋል።