በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲቆሙ በተጠሩ ሰልፎች ላይ ግጭት ተፈጠረ

በቱርክ እና በሜክሲኮ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ይቁም በሚል በተጠሩ ሰልፎች ላይ ፖሊሶች አስለቃሽ ጋዝና ጭስ በመጠቀም ለመበተን ሞክሯል።

በሜክሲኮ ጓይማስ ከተማ በከተማዋ ሴት ከንቲባ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ሶስት ሰዎች በጥይት ተገድለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በቱርኳ መዲና ኢስታንቡል ከተማ ሰልፈኞች ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመጋጨታቸው ረብሻ ተቀሰቅሷል።

በባርሴሎና፣ ፓሪስ እና ለንደን ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለማስወገድ ዓለም አቀፍ ቀኑን ምክንያት በማድረግ ትልልቅ ሰልፎች ተካሂደዋል።

በሜክሲኳዋ ጓይማስ ታጣቂዎች የከተማዋን ማዘጋጃ ቤት ዘልቀው በመግባት አንዲት ሴት ተቃዋሚና የመንግሥት ሰራተኛ የሆነ ግለሰብና የከንቲባዋ ካርላ ኮርዶቫን ጠባቂ ተኩሰው መግደላቸውን የሃገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

የአይን እማኞች ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከመተኮሱ በፊት በህንፃው በር ላይ ፈንጅ የሚመስል ድምፅ እንደተሰማ ነው።

የአጥቂዎቹ ማንነት እና ዓላማ እስካሁን አልታወቀም።

በሜክሲኮ ከተማ በነበረው ሰልፍ ላይ በርካቶች ሴቶች በፆታቸው ምክንያት የሚገደሉበትን ጥቃት 'ፌሚሳይድ' በመቃወም 'አንድ ሴትም ቢሆን መቀነስ' የለባትም ሲሉ ተደምጠዋል።

"ሁልጊዜ እንቃወማለን እናም ነገሮች በዚህ መንገድ መቀጠል የለባቸውም። በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት የሆነ ወቅት ላይ መቆም አለበት" በማለት ላውራ ቫሌ የተባለች ተቃዋሚ ለሮይተርስ የተናገረች ሲሆን አክላም "ሴቶች ጥቃት በሚደርስብን ወቅት ሪፖርት ስናደርግ ባለስልጣናቱ እርምጃ ሲወስዱ አናይም" ብላለች።

ፖሊስ መዶሻ በያዙ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃጭ ጋዝ ረጭቷል።

በላቲን አሜሪካ አገራት በየቀኑ ቢያስ 10 ሴቶች እና ታዳጊ ሴቶች እንደሚገደሉ የአምነስቲ መረጃ ያመላክታል።

"ሜክሲኮ የሴት ገዳይ! እየገደሉን ነው!" በማለት አንዲት ሴት ከፖሊስ ጋር በነበረ ፍጥጫ ጮክ ብላ ስትናገር ተሰምቷል።

አንዳንድ ፊታቸውን የሸፈኑ ሰልፈኞች ጠርሙሶችን፣ድንጋዮችን እና በፖሊሶች ላይ እንደወረወሩ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በሰልፉ ላይ 10 ሴት የፖሊስ አባላትን ጨምሮ 17 ሰዎች ቆስለዋል ሲል ፖሊስ ተናግሯል።