በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሚደረግ ጫናን የሚቃወሙ ሰልፎች በበርካታ አገራት ተደረጉ

በዩናይትድ ኪንግደም ለንዶን ከተማ የተደረገ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, @fitsumaregaa

የምስሉ መግለጫ, በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ከተማ የተደረገ ሰልፍ

ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በሰሜን አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና እስራኤልን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች የምዕራብ አገራትን ጫና በመቃወም ለኢትዮጵያ መንግሥት ያላቸውን ድጋፍ አደባባይ በመውጣት ገለጹ።

ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት አማጺያን ጋር በሚያደርገው ጦርነት ምዕራባውያን አገራት ለፌደራሉ መንግሥት ድጋፍ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

መንግሥታዊው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በ27 ከተሞች የድጋፍ ሰልፉ መካሄዱን ዘግቧል።

የድጋፍ ሰልፉ ከተደረገባቸው ከተሞች መካከል፤ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ኒው ዮርክ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ኦስቲን፣ ሂውስተን፣ ቶሮንቶ፣ ኦታዋ፣ ካልጋሪ፣ ዊኒፒግ እና ለንደን ተጠቃሽ ናቸው።

የካናዳው ሲቢኤስ ኒውስ በካናዳዋ ማኒቶባ ግዛት ዊኒፒግ ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት ጋር በሚያደርገው ጦርነት የካናዳ መንግሥት ለኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ አደባባይ ወጥተው ጠይቀዋል ሲል ዘግቧል።

በዊኒፒግ ከተማ የተዘጋጀውን የድጋፍ ሰልፍ ካስተባበሩት መካከል አንዱ የሆኑት ማርቆስ ተገኝ፤ "በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ በተለይ አሜሪካ ጣልቃ መግባት ማቆም አለባት፤ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው እንዲፈቱ መፍቀድ አለባት" ሲሉ ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

በሌላኛዋ የካናዳ ከተማ ካልጋሪ ተመሳሳይ የድጋፍ ሰልፍ መካሄዱን ሲቲቪ ኒውስ ካልጋሪ ዘግቧል። ለፌደራሉ መንግሥት ድጋፍ ለመስጠት በተጠራው ሰልፍ ላይ ሰዎች #NoMore (ከአሁን በኋላ ይብቃ) እንዲሁም #Handsoff (እጃችሁን አንሱ) የሚሉ መፈክሮችን ይዘው መውጣታቸው ሲቲቪ ኒውስ ካልጋሪ አሳይቷል።

በተመሳሳይ በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ኦስቲን ከተማ ተመሳሳይ ድጋፍ አድርገዋል። "እነዚህ በኢትዮጵያ ያሉ ጉዳዮች ናቸው፤ እራሳችን መፍታት እንችላለን። እዚህ የተገኘነው እባካችሁ አቁሙ፤ የራሳችንን ጉዳይ እራሳችን እንፈታዋለን ለማለት" በማለት የኦስቲን ሰልፍ ተሳታፊ የሆነው ቴድ ኃይሉ ለሲቢኤስ ኦስቲን ተናግሯል።

በኦታዋ ካናዳ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, @MFAEthiopia

የምስሉ መግለጫ, በኦታዋ ካናዳ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱ ሰልፎችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን በማጋራት "...ለእውነት ለቆሙ ኢትዮጵያውያን እና የአፍሪካ ቀንድ ዳያስፖራዎች አድናቆቴን እገልጻለሁ" ብለዋል።

በየአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ፍጹም አረጋ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች በኢትዮጵያውያን መንግሥትን በመደገፍ ሰልፍ የተደረገበትን የትናንቱን ቀን "በኢትዮጵያ የዲያስፖራ ታሪካዊ ቀን ነው" ሲሉ ትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

በአውሮፓ እና አሜሪካ በሚገኙ ከተሞች ከተደረጉት የድጋፍ ሰልፎች በተጨማሪ፤ በትዊተር ላይ ሰዎች ደምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ ይዘው የወጡት #Handsoff መፈክር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ጊዜ ሪትዊት ተደርጓል።

የው ጣልቃ ገብነት

የፌደራሉ መንግሥት ከህወሓት አማጺያን ጋር እያደረገ ያለው ጦርነት በድርድር እንዲፈታ ምዕራባውያን አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።

የአሜሪካ መንግሥት አስተዳደር ጦርነቱ ይቁም ከማለት ባሻገር በጦርነቱ ተሳታፊ ናቸው አልያም ጦርነቱ እንዲራዘም ምክንያት ናቸው ባለቸው ግለሰቦች ላይ እቀባ መጣሉ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል ያለቻቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያን ብዙ ከምትጠቀምበት ከአጎዋ የንግድ ስምምነት ለማገድ መወሰኗ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ወደ ትግራዩ ጦነርት ተገዶ መግባቱን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

ምዕራባውያን በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት እንዲቆምና ሰብአዊ እርዳታ በችግር ላይ ላሉ ሰዎች ያለገደብ እንዲደርስ ጫና እያደረጉ መሆናቸውን ቢገልጹም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ለአማጺያን ድጋፍ በማድረግ የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ እየሞከሩ ነው ሲል ይከሳል።