የኢንፎርሜሽንና የመገናኛ መሳሪያዎች ያላቸው ተቋማትና ግለሰቦች እንዲያስመዘግቡ ታዘዙ

የመገናኛ መሳሪያ

የፎቶው ባለመብት, Insa/fb

የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) በአገሪቱ የተለያዩ የኢንፎርሜሽን እና የመገናኛ መሳሪያዎች ያሏቸው ግለሰቦችና ተቋማት በሁለት ሳምንት ውስጥ እንዲያስመዘገቡ አዘዘ።

ኤጀንሲው ምዝገባውን ማድረግ ያስፈለገው "በአገሪቱ ህልውና ላይ የሚያጋጥም አደጋን እንዲሁም የተደቀነባትን የግዛት አንድነት ስጋት እና የሉአላዊነት ጥሰትን ለመከላከል ሁሉን አቀፍ የጥንቃቄ እርምጃዎች መውስድ አስፈላጊ በመሆኑ" ነው ብሏል።

ተቋሙ አርብ ኅዳር 11/2014 ዓ.ም ባቀረበው ጥሪ በሕግ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን የኢንፎርሜሽንና የኮሚዩኒኬሽን መሳሪያዎች ሲመዘግብ መቆየቱን አመልክቶ እነዚህ መገልገያዎች በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ይዞታ ለማወቅ ምዝገባው እንዳስፈለግ ገልጿል።

ጨምሮም አሁን ምዝገባ የሚደረገው እነዚህ በአገር ውስጥ ያሉ የኮሚዩኒኬሽን መሳሪያዎች "በአሸባሪዎች እና በግብረ አበሮቻቸው አማካይነት ለሽብር አላማ እንዳይውሉ" ለማድረግ በድጋሚ በመመዝገብ መሳሪያዎቹ በሚመለከታቸው አካላት እጅ ስለመኖራቸው ማወቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ብሏል።

በዚህም መሠረት የጦር ሜዳ መነጽር፣ ኮምፓስ፣ የጂፒኤስ መሳሪያ፤ ወታደራዊ እና ሲቪል የመገናኛ መሳሪያዎች መገናኛ ሬዲዮ፣ ሳተላይት ስልክ፣ ቪሳት እና ቢጋን እንዲሁም ድሮኖች ያሏቸው ግለሰብ፣ መንግሥታዊና የግል ተቋማት፣ ኤምባሲዎች፣ ዲፕሎማቶች በአስራ አምስት ቀን ውስጥ እንዲያሳውቁ ጥሪ አቅርቧል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ባወጣው ማሳሰቢያ ላይ እነዚህን መሳሪያዎች በግለሰቦችም ሆነ በተቋማት ይዞታ ስር ጥቅም ላይ ሲውሉ የተመለከተ ማንኛውም ሰው ጥቆማ እንዲያደረግ ጥሪ አቅርቧል።

በመላው አገሪቱ በቅርቡ ከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኋላ በተለያዩ ስፍራዎች ፖሊስ ባካሄዳቸው ፍተሻዎች የተለያዩ የኮምዩኒኬሽን መሳሪያዎችን ማንኘቱን አሳውቋል።