ኢትዮጵያ የምታከናውነው ድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት ክትባት ምንድነው?

የእንስሳት ክትባት
የምስሉ መግለጫ, የእንስሳት ክትባት

በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር አካባቢዎች ድንበር ተሻጋሪ ተዛማች የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሁለተኛው ዙር የእንስሳት ክትባት ዘመቻ እየተካሄደ ይገኛል።

የክትባት ዘመቻው በኢትዮጵያ በኩል በቦረና ዞን፣ ሞያሌ ወረዳ የተለያዩ እንስሳትን በመከተብ የተጀመረ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ በኬንያ በኩል ይካሄዳል።

ይህ ከአጎራባች አገራት ጋር በመቀናጀት የሚካሄደው ድንበር ተሻጋሪ የክትባት ዘመቻ በደቡብ ኦሞ ዞን፣ በሀመር ወረዳም በይፋ ተጀምሯል።

አርብቶ አደሮች ግጦሽና ውሃ ፍለጋ ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ አጎራባች አገራት ተቀናጅተው ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን በጋራ መከላከልና መቆጣጠር ካልቻሉ በድንገት የሚከሰቱ በሽታዎች የእንስሳትን ምርታማነት ከመቀነሰ አልፎ ቁጥራቸውንም በጊዜ ብዛት ይቀንሰዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር እንደሚለው የእንስሳት ሀብት ልማት ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ዝሪያን በማሻሻል፣ በቂ መኖን በማቅረብ እና ገበያን በማመቻቸት ብቻ ሳይሆን ከጤናማ እንስሳት ጤናማ ምርት ማቅረብ ሲቻል ነው።

በአርብቶ አደሩ አካባቢ የእንስሳት በሽታዎችን በመካለከል እና በመቆጣጠር ጥራት ያለውን የእንስሳት ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ በሆነ መልኩ ማቅረብ ዋነኛ አላማው ነው።

የድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታ ክትባትን በጋራ የመተግበር ሥራ በተለይ በአራት ዋና ዋና በሽታዎች ላይ ያተኮረ እንደሆነ በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒትር ዴኤታ አማካሪ የሆኑት ዮሐንስ ግርማ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"ከኬንያ ጋር በተለይ አራት ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ስምምነት ላይ ደርሰናል። የመጀመሪያው የበጎችና የፍየሎች ደስታ መሰል በሽታ ክትባት ነው። ሁለተኛው ደግሞ የበጎችና የፍየሎች የሳምባ በሽታ ክትባት፣ የከብቶች የሳምባ በሽታ እንዲሁም በግመሎች ላይ የሚከሰቱ ዋና ዋና በሽታዎችን ነው አንድ ላይ የምንከትበው" ይላሉ።

በአውሮፓውያኑ 2019 የተጀመረው ይህ ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን በጋራ የመከላከል ሥራ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ በያዝነው ዓመት ደግሞ በአዲስ መልኩ ነው እየተሠራ የሚገኘው።

ምንም እንኳን የግብርና ሚኒስቴር በተለይ ከኬንያ መንግሥት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ከሁለት ዓመት በፊት የድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን ክትባት መስጠት ቢጀምርም፤ ባለፈው ዓመት ግን ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ በተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች ምክንያት ሥራውን ማስቀጠል አልተቻለም።

ነገር ግን በያዝነው ዓመት ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ በኩል በቦረና ዞን፣ ሞያሌ ወረዳ ክትባቱን ያካሄደ ሲሆን በኬንያ በኩል ደግሞ በመርሳቢት ካውንቲ ተካሂዷል። በመቀጠል በደቡብ ኦሞ ዞን፣ በሐመር ወረዳ እንዲሁም በሰሜን ኦሞ ዞን የእንስሳት ክትባቱ ተካሂዷል።

በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ካለው የንግድ ትስስር አንጻር እና በሁለቱም አገራት የሚገኙ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ይዘው መንቀሳቀሳቸው እንስሳቱን ለድንበር ተሻጋሪ በሽታዎች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

ዮሐንስ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ "ምናልባት እኛ በራሳችን በኩል ያሉትን እንስሳት ብቻ ከትበን ብንተውና በሌላኛው በኩል በተመሳሳይ እንስሳቱን ባይከትቡ የበሽታዎቹን ስርጭት መቆጣጠር አንችልም።"

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እንስሳቱ ከአንዱ አገር ወደሌላኛው መንቀሳቀሳቸው ነው።

ይህ የክትባት ስምምነት የተደረገው ከኬንያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ እና ከሱዳን ጋር ነው።

ከዚህ በፊት በተደረጉ ድንበር ተሻጋሪ ተዛማች የእንስሳት ክትባት ዘመቻዎች በርካታ እንስሳት መከተባቸውን የገለጹት ዶ/ር ዮሐንስ፤ በዚህኛውም ዙር የተሻለ ውጤት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

"በዋነኛነት የምናተኩረው እነዚህ በሽታዎች በድንገት እንዳይከሰቱ ማድረግ ላይ ነው። አብዛኞቹ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክም ሆነ በሌላ መልኩ የሚከሰቱባቸው ወቅቶች አሉ። እነሱን ተንተርሰን ከመከሰታቸው ቀደም ብለን ዘመቻዎች እናደርጋለን። አሁን ካለው የድርቅ ክስተት ጋር ተያይዞ እንስሳት ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም የበሽታዎች ክስተት ግን በብዛት እየታየ አይደለም" ይላሉ።

በአጠቃላይ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያን በሚያዋስኑና ስምምነት ካደረጉ አገራት ጋር አጎራባች በሆኑ አካባቢዎቸ እስከ 5.4 ሚሊየን እንስሳትን ለመከተብ ዕቅድ መያዛቸውን አማካሪው ይናገራሉ።

በያዝነው ዓመት የሴንትራል ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በሠራው ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ ወደ 61 ሚሊየን የሚጠጉ የቀንድ ከብቶች አሏት። ከ40 ሚሊየን በላይ ፍየሎችና ከ50 ሚሊየን በላይ በጎች እንዲሁም 8 ሚሊየን የሚደርሱ ግመሎችም አሏት።

አርብቶ አደሩ የሚያረባቸውና የሚጠቀማቸው አብዛኛዎቹ የእንስሳት ዝርያዎች በተፈጥሯቸው በሽታን የመቋቋምና አስቸጋሪ የአየር ፀባይን መቋቋም የሚችሉ ናቸው።

የግብርና ሚኒስቴር እንደሚለው እነዚህ ዝርያዎች በሽታና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም ቢችሉም ምርትና ምርታማነት ላይ ግን ችግር አለባቸው።

ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባትም ሚኒስቴሩ ከክትባቶች በተጨማሪ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚገኙት እንስሳት ላይ ማሻሻያ በማድረግ የተሻለ ምርት መስጠት እንዲችሉ እየሠራ መሆኑን ዮሐንስ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

"በቦረና ዞን የሚገኘው የዝርያ ማሻሻያ ማዕከል ውስጥ የቦረና ዝርያዎችን በማባዛት፣ በማሻሻልና በመጠበቅ ሥራዎችን ይሠራል። ቁጥራቸው ሲበዛ ደግሞ ለአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲከፋፈሉ ይደረጋል። ወደሌሎች የአገሪቱ አርብቶ አደር አካባቢዎችም እንዲደርሱ ይደረጋል" ብለዋል።

በድንበር አካባቢዎች ላይ ከሚደረገው የክትባት ዘመቻ በተጨማሪ በመላው አገሪቱ የሚገኙ እንስሳት ላይ ክትባቱ ይቀጥላል። ነገር ግን በድንበር አካባቢዎች ላይ የሚገኙ እንስሳት ቁጥራቸው ላቅ ያለ መሆኑ እና ከቦታ ቦታ ስለሚንቀሳቀሱ ቅድሚያ ተሰጥቶ ይከተባሉ።

እነዚህ በሽታዎች ቀስ በቀስ ሲጠፉና የእንስሳቱን ደኅንነት መጠበቅ ከተቻለ በዓለም አቀፍ ደረጃ የገበያ ተወዳዳሪነትን ለመጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

"እነዚህ በሽታዎች በኢትዮጵያ አሉ ተብሎ ከታሰበ ምርታችንን ማንም አይገዛም፤ አልያም ቁጥሩ ዝቅተኛ ይሆናል። በተለይ በርካታ ያደጉ አገራት እነዚህን በሽታዎች ማጥፋት በመቻላቸው በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ ሆነዋል። እኛም እነዚህም በሽታዎች ማጥፋት ስላልቻልን ወደ አውሮፓ እና እስያ ገበያዎች መድረስ አልቻለንም" ሲሉ ያስረዳሉ።

ዓለም አቀፍ የእንስሳት ጤና ድርጅት የሚባለውና 182 አባል አገራት ያሉት ተቋም በየጊዜው የአገራትን የእንስሳት ጤና የሚከታተልና የአገራቱን ደረጃ የሚያወጣ ነው። ኢትዮጵያም የዚህ ድርጅት አባል እንደመሆኗ የእንስሳቶቿን ጤንነት ከጠበቀች የምታገኘው ተቀባይነት ከፍተኛ እንደሆነም ይናገራሉ።

ይህ ክትባት የዓለም አቀፍ ገበያውን ከመድረስ ባለፈም አርብቶ አደሮች በበቂ ሁኔታ ከእንስሳቶቻቸው ተገቢውን ምርት እንዲያገኙ እና የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።