በሴቶች የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የደቡብ አፍሪካዋ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የመጀመሪያውን ዋንጫን አነሳች

ማሜሎዲ ሰንዳውንስ

የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የጋናውን ሃሳካስ ሌዲስን 2 ለ 0 በማሸነፍ ካይሮ ላይ የተካሄደውን የመጀመሪያውን የሴቶች የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ በማንሳት ታሪክ አስመዘገቡ።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሁለቱም ቡድኖች ኳስ ተቆጣጥረው ተጫውተዋል። አንዳንድ ደካማ ቅብብሎች መኖራቸው በሁለቱም በኩል ግልጽ የጎል ዕድሎችን መፍጠር እንዳይችሉ አድርጓል።

ሰንዳውንስ በሰባተኛው ደቂቃ ሊራቶ ክጋሳጎ ከፍጹም ቅጣት ክልል ውጪ የሞከረችውን የቅጣት ምት ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።

የመጀመሪያው ጎል የተገኘው በ32ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ሦስቱ የሰንዳውንስ አጥቂዎች በጥሩ ሁኔታ ተቀናጅተው ሃሳካሶች ላይ ጎል አስቆጥረዋል። ቹዬኔ ሞሪፊ ደግሞ የግቧ ባለቤት ናት።

የደቡብ አፍሪካው ቡድን በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን በመቆጣጠር በ65ኛው ደቂቃ ላይ በማግኮይ አማካይነት ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል።

ሃሳካሶች በ76ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ ቢያደርጉም የሰንዳውንስ በረኛ አድናዋለች።

ጋናዎች ጎል ለማግኘት ሲያጠቁ በመከላከሉ ረገድ ቢሳሱም ሰንዳውንሶች ዕድሉን ተጠቅመው ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር አልቻሉም።

ሰንዳውንሷ ሬጂና ማጎሎላ ተቀይራ ከገባች ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተባራለች።

የፍጻሜው ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ያልተጠበቀ ነበር። ሰንዳውንሶች ለፍጻሜው እስኪደርሱ ሁለት ግቦችን ብቻ ሲያስቆጥሩ ሃሳካሶች ደግሞ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች 10 ጎሎችን ማስቆጠር ችለው ነበር።

ከፍጻሜው በፊት የማሜሎዲ ሰንዳውንስ አሰልጣኝ ጄሪ ሻባላላ ተመሳሳይ ውድድሮችን "ተከላካዮች ያሸንፋሉ" ብለው ነበር።

በውድድሩ ግማሽ ፍጻሜ በመለያ የፍጹም ቅጣት ምት ወቅት ካልሆነ በስተቀር ቡድናቸው አንድም ጎል አለማስተናገዱ አስተያየቱ ትክክል መሆኑን አሳይቷል።

በውድድሩ ሃሳካስን ካስቆጠራቸው ጎሎች ግማሹን ያስቆጠረችው የ19 ዓመቷ ኤቭሊን ባዱ የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ብትሆንም በፍጻሜው ጨዋታ ግን ጎል ማስቆተር ሳትችል ቀርታለች።

ሐሙስ የሞሮኮው አስ ፋር የኢኳቶሪያል ጊኒው ማላቦ ኪንግስን 3 ለ 1 በማሸነፍ ሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል።