ካማላ ሐሪስ የመጀመሪያዋ ሴት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ለአንድ ሰዓት ተኩል መሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካማላ ሐሪስ በአሜሪካ ታሪክ ለ85 ደቂቃዎች ያህልም ቢሆን አገሪቱን በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት ሆኑ።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ ሐሪስ የፕሬዝዳንትነት መንበሩን የጨበጡት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሕክምና ላይ ስለነበሩ ነው።
ባይደን ለሕክምና የማደንዘዥ መድኃኒት መውሰዳቸውን ተከትሎ ሥልጣናቸውን ለ57 ዓመቷ ምክትላቸው ሐሪስ አስተላልፈው ነበር።
የባይደን ሐኪም ፕሬዝዳንቱ ደህና እንደሆኑና ወደ ሥራቸው መመለስ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ባይደን 79ኛ ዓመት ልደታቸውን ከሰሞኑ ያከብራሉ።
ፕሬዝዳንቱ ሕክምና ላይ በነበሩበት ጊዜ ምክትሏ ሐሪስ ከዋይት ሐውስ የምሥራቅ ክንፍ ካለው ቢሯቸው ሥራቸውን ሲያከናውኑ ነበር ተብሏል።
ካማላ ሐሪስ ለአጭር ጊዜ በቆየው የመሪነት ሥልጣናቸው የመጀመሪያዋ ሴት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ብቻ ሳይሆኑ የመጀመሪያዋ ጥቁር እና ደቡብ እስያዊት ሴት ፕሬዝዳንትም ናቸው።
በጊዜያዊነት የመሪነት ሥልጣንን ማስተላለፍ በአሜሪካ ሕገ መንግሥት የተለመደ እንደሆነ የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ተናግራለች።
ከዚህ በፊት እአአ በ2002 እና 2007 ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ሕክምና ሲያደርጉ ሥልጣናቸውን ለምክትላቸው አስተላልፈው ነበር።
የጆ ባይደን ሐኪም ኬቨን ኦኮነር "የ78 ዓመቱ መሪ ጤናማና ጠንካራ ናቸው። ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይችላሉ" ብሏል።
ባይደን ከሆስፒታል ወደ ዋይት ሐውስ ሲመለሱ "ጥሩ ስሜት ይሰማኛል" ብለው መናጋረቸው ተዘግቧል።
ባይደን በአሜሪካ ታሪክ በዕድሜ ትልቁ መሪ ናቸው። አምና ሕክምና ሲደረግላቸው "ጤናማ እና ብርቱ" ተብለዋል።












