ነጭ ሴት ደፍረዋል ተብለው በስህተት የተከሰሱ አራት ጥቁር አሜሪካዊያን ከ70 ዓመታት በኋላ 'ነጻ' ወጡ

ይቅርታ የተደረገለት ዋልተር ኢርቪን ከጠበቆቹ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንደ አውሮጳዊያኑ የጊዜ ቀመር በ1949 ዓ/ም አራቱ ጥቁር አሜሪካዊያን አንዲት ነጭ ልጃገረድ ጠልፎ፣ በመድፈር ነበር የተከሰሰቱት፡፡

ይህም በአሜሪካ ማዕከላዊ ፍሎሪዳ ግዛት፣ ግሮቭላንድ ከተማ ነበር የሆነው፡፡

አራቱ ተከሳሾች ቻርለስ ግሪንሊ፣ ዋልተር ኤርቪን፣ ሳሜኤል ሼፐርድ እና ኤርነስት ቶማስ ይባላሉ፡፡ በቅጽል ስማቸው ‹‹ዘ ግሮቭላንድ ፎር›› በሚል ይጠራሉ፡፡

እነዚህ አራት ተከሳሾች ከብዙ ዓመታት በኋላ በፍሎሪዳ ግዛት በጥር 2019 ምሕረት ተደርጎላቸው የዓለም መነጋገሪያ ነበር፡፡ አንዳቸውም ግን ይህን ምሕረት ለማየት አልታደሉም፡፡

አራቱ ጥቁር ተከሳሾች ያኔ ክሱ ሲመሰረትባቸው ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 26 ይሆን ነበር፡፡ ከሰባት ዐሥርታት በኋላ ግን በነዚህ ጥቁር አሜሪካዊያን ላይ የተመሠረተው ክስ በሐሰት መረጃዎች የተቀነባበረ እንደነበረ ተደርሶበታል፡፡

ከአራቱ አንዱ የሆነው ወጣቱ ቶማስ በወቅቱ በድርጊቱ በተቆጡ አንድ ሺህ ሰዎች ታድኖ ከተያዘ በኋላ የደቦ ጥቃት ተፈጽሞበት በመቶ ጥይቶች ተደብድቦ ነበር የተገደለው፡፡

ሌሎች ደግሞ ታስረው በነበሩት ቦታ ገና ወደ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው ነበር፡፡

ፍርድ ቤት ሲቀርቡም ጉዳያቸውን ይመለከቱ የነበሩ ዳኞችም ሆኑ ዐቃቢያን በሙሉ ነጮች ነበሩ፡፡

ከሦስቱ ቀሪ ተከሳሾች መሀል ደግሞ ሳሙኤል ሼፐርድ በኋላ ላይ ወደ ፍርድ ቤት በሚያመላልሰው ነጭ ፖሊስ በጥይት ተደብድቦ ተገድሏል፡፡

ኤርቪን በበኩሉ ዕድሜ ይፍታህ ከተፈረደበት በኋላ ረዥም ዓመት በእስር ቆይቶ በይቅርታ በተፈታ በዓመቱ በ1969 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

ግሪንሊም እንዲሁ ዕድሜ ይፍታህ ከተፈረደበት በኋላ በ1962 በይቅርታ ተፈትቶ በ2012 ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው፡፡

ይሁንና ከረዥም ጊዜ በኋላ ጉዳዩን በድጋሚ የመረመቱት የፍሎሪዳ ዳኛ የኤርነስት ቶማስን እና የሳሙኤል ሼፐርድን ክስ ውድቅ አድርገውታል፡፡ በቻርለስ ግሪንሊን እና የበዋልተር ኢርቪን ተከፍተው የነበሩ ክሶችም ትክክል እንዳልነበረ ፈርደዋል፡፡

በወቅቱ በተከሳሾቹ ቀርቦ የነበረው መረጃ በውስጥ ሱሪያቸው የወንድ ፈሳሽ ታይቷል የሚል ሲሆን ይህ ግን ቅንብር እንጂ እውነት እንዳልነበረ ከብዙ ምርመራ በኋላ ተደርሶበታል፡፡

ይህን ዜና የሰሙት የተከሳሽ ቤተሰቦች በእንባ ተራጭተዋል፡፡

ምንም እንኳ አንዳቸውም ተከሳሾች ይህን ለመስማት በሕይወት ባይኖሩም ጉዳዩ ሌሎች በቆዳ ቀለማቸው የተነሳ በስህተት የተከሰሱ ጥቁሮችን ተስፋ የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡ የዚህ ውሳኔ መወሰን ሌሎች ጥቁሮችም ጉዳያቸው በድጋሚ እንዲታይ ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሏል፡፡

" እኛ የተባረክን ነን፡፡ ይህ የመጀመርያ እንጂ የመጨረሻ አይሆንም፡፡ ይህን ዕድል ያላገኙ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ብዙ ቤተሰቦች ይህን ዕድል ለማየት አልታደሉም፡፡ ምናልባት ወደፊት ያዩት ይሆናል" ብላለች የቶማስ ቤተሰብ እንባ እየተናነቃት፡፡

ያኔ ድሮ በ16 ዓመቱ በሐሰት ተከሶ የነበረው የቻርለስ ግሪንሊ ሴት ልጅ ካሮል ግሪንሊ በበኩሏ ይህን ዜና ስትሰማ እጅግ ስሜታዊ በመሆን ስታለቅስ ነበር፡፡ ራሷን በመሳት ስትወድቅም አጠገቧ ያሉ ሰዎች አቅፈው አረጋግተዋታል፡፡

‹‹መቼም ቢሆን ላመናችሁበት ነገር እስከመጨረሻው ቁሙ›› ስትል ተናግራለች፡፡

የአካባቢው አቃቢ ሕግ ሪፐብሊካኑ ቢል ግላድሰን ፋይሉን እንዲንቀሳቀስና አራቱ ጥቁሮች በይፋ ነጻ እንዲሆኑ ያደረጉት ባለፈው ወር ነበር፡፡

‹‹መረጃዎችን በድጋሚ በማየት ወዴት እንደሚወስደን መረመርን፡፡ ምርመራችን እዚህ ውሳኔ ላይ አደረሰን›› ብለዋል ከ70 ዐመታት በፊት ክሱ በተሰማበት ፍርድ ቤት በር ላይ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፡፡

በ2017 የፍሎሪዳ ግዛት አስተዳደር ለአራቱ ተከሳሽ ቤተሰቦች በይፋ የይቅርታ ደብዳቤ ያቀረበ ሲሆን በሕግ ከሞት በኋላ የሚሰጥ ምሕረት እንዲደረግም ለፍርድ ቤት ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡

የነዚህ አራት ጥቁሮች በስህተት መወንጀልና መሞትን የተመለከተ ‹‹ዴቪል ኢን ዘ ግሩቭ›› የሚል መጽሐፍ ተጽፎበታል፡፡ መጽሐፉ የ2013 የዝነኛው የአሜሪካዊያኑ ፑሊትዘር ሽልማት አሸናፊ ሆኖ ነበር፡

ጥቁሮቹን የከሰሷቸው ዳኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images