ጨቅላ ህጻንትን በጥንቃቄ ማሸት (ማሳጅ) ህይወታቸውን እንደሚታደግ ያውቃሉ?

የረኑ ሳክና ልጅ የተወለደችው በ36 ሳምንቷ ነው።

ከ9 ወር ከ5 ቀን ቀድማ የተወለደችውን ጨቅላ ረኑ ወደ ቤቷ ይዛት ስትገባ 2.4 ኪሎ ግራም ነበር የምትመዝነው።

ረኑ ልጇን ስትመለከታት አሳሳቻት። ትንሽ ናት። ቆዳዋም ስስ ነው።

የረኑ ቤተሰቦች ጨቅላዋ ቶሎ እንድትፋፋ በሕንድ የተለመደ ሕክምና ማግኘት አለባት አሉ።

ሕክምናው በየቀኑ ልጆችን ማሸት (ማሳጅ ማድረግ) ነው። በሕንድ ማኅበረሰብ ዘመናት የተሻገረ ልማድ ነው።

የረኑ ልጅ ሐኪሞች ግን እምብዛም በማሳጁ አላመኑበትም። ጨቅላዋ ሰውነቷ ሳይጠነክር ማሳጅ እንዳትደረግ ወሰኑ።

ረኑ በቤተሰቦቿ እና በሐኪሞቹ ምክር መካከል ያለ ውሳኔ ላይ ደረሰች። ልጇ ሁለት ሳምንት ሲሞላት ማሳጅ ለመጀመር ነበር ውሳኔዋ።

ነገር ግን ልጇ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሰውነቷ አልጨመረም። እንቅልፍም አትተኛም ነበር።

ረኑ ነገሩ ሲያሳስባት ለልጇ ጡረታ የወጡ ነርስ ቀጠረች። ነርሷ ጨቅላዋ ማሳጅ እንድትደረግ አዘዙ።

ብዙም ሳይቆይ ልጅቷ ሰውነቷ ይፋፋ ጀመር። እንቅልፏም ተስተካከከለ።

ልጆችን ማሳጅ ማድረግ ምን ይጠቅማል?

በደቡብ እስያ ባህል ጨቅላ ልጆችን ማሳጅ ማድረግ የተለመደ ነው። አሁን ደግሞ በሳይንሱ ይህን ልማድ የሚደግፉ ጥናቶች ወጥተዋል።

ልጆችን ማሳጅ ማድረግ የሰውነት ክብደታቸውን ይጨምራል፣ የባክቴሪያ ኢንፌክሽንን ይከላከላል፣ የጨቅላ ሞትን 50 በመቶም ይቀንሳል።

ወላጆች ከሐኪሞች ጋር በመማከር ሕክምናውን ለልጆቻው መስጠት ይችላሉ።

በሕንድ፣ ኡታር ፓርዲሽ የተወለደችው ረኑ የማስታወቂያ ባለሙያ ናት። ቤተሰቦቿ በዘልማድ የነገሯትን ሕክምና ከሳይንስ ማረጋገጫ አግኝታበታለች።

በሕንድ ባህል ጨቅላ ልጅ ብቻ ሳይሆን እናትም እንደወለደች ማሳጅ ትደረጋለች።

"እናቴ እኔን ከወለደች በኋላ እንዴት በፍጥነት እንዳገገመች ስጠይቃት ማሳጅ እንደተደረገች ነግራኛለች" ትላለች ረኑ።

እሷም ልማዱን ከእናቷ ወርሳ ልጇ ላይ ተግብራዋለች።

ለልጇ የቀጠራቸው ነርስ እንዴት የማሳጅ ዘይት እንደሚሞቅ አስተምረዋታል። ዘይቱ የኮኮናት ወይም አልመንድ ሊሆን ይችላል።

ዘይቱ ለብ ካለ በኋላ የጨቅላ ሆድ ለግማሽ ሰዓት ይታሻል። በየቀኑ ለ30 ደቂቃ ማሳጁ ከተደረገ በኋላ ልጅ ሙቅ ሻወር ይወስዳል።

የታመቀ ጋዝን ለማስተንፈስ ከአናታቸው እስከ እግር ጣታቸው ድረስ ይታሻሉ" ስትል ታስረዳለች።

ልጆችን ማሳጅ ማድረግ እስከ ወጣትነታቸው የሚዘልቅ ጥቅም እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የአእምሮ እና እድገት ባለሙያው ጌሪ ዳርምስታድት እንደሚለው፤ የሰዎች ቆዳ ከፍተኛ እንክብካቤ የሚፈልግ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ችላ ይባላል።

በሕንድ እና በባንግላዲሽ እናቶች እና አያቶች ጨቅላ ልጆችን ማሳጅ እንደሚያደርጉ ይናገራል።

"ለዘመናት የዘለቀው ልማድ ያስደንቀኝ ስለነበር ምርምር አድርጌበታለሁ" ይላል።

እአአ በ2008 በተሠራ ጥናት፤ ልጆችን ማሳጅ ማድረግ ሕይወታቸውን እንደሚታደግ ተደርሶበታል። ጥናቱ የተሠራው በ497 ጨቅላ ልጆች ላይ ባንግላዲሽ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ነው።

የጨቅላ ልጆችን ሞት መቀነስ

ጌሪ እንደሚለው፤ ማሳጅ የጨቅላ ልጆችን ሞት እንደሚቀንስ ተደርሶበታል።

"በኢንፌክሽን የመጠቃት ዕድልን በ40 በመቶ እና ሞትን ከ25 አስከ 50 በመቶ ይቀንሳል" ይላል።

ማሳጅ ሰውነት እራሱን ከበሽታ የሚከላከልበትን ጉልበት ያዳብራል። በኢንፌክሽን ላለመያዝም ይረዳል።

መመንመን የገጠማቸው ልጆች ማሳጅ ሲደረጉ ሰውነታቸው ማይክሮባዮም እንደሚያዳብር ባለሙያው ያስረዳል።

ለማሳጅ ጥቅም ላይ የሚውለው ዘይት ቆዳን ስለሚያጠነክር ባክቴርያ በቀላሉ ወደ ሰውነት ዘልቆ አይገባም። ባክቴርያ ወደ ሰውነት ካልገባ ደግሞ ሕይወት የሚቀጥፉ በሽታዎችን መከላከል ይቻላል።

ለባለሙያው ከጥናት ቡድን ጋር በመሆን 26ሺህ ልጆች ላይ ነበር ምርምር ያደጉት።

ግማሹ በሱፍ ዘይት የተቀሩት ደግሞ በሰናፍጭ ዘይት ማሳጅ ከተደረጉ በኋላ በተሠራ ጥናት መሠረት ልጆቹ እድገታቸው መሻሻል አሳይቷል።

ከልጆቹ መካከል ሲወለዱ የተመጣጠነ የሰውነት ክብደት ያላቸው ለሞት የመጋለጥ መጠናቸው አልተመዘነም።

በሌላ በኩል ሲወለዱ ከመደበኛው ክብደት ያነሱ ልጆች ማሳጅ ተደርገው ለሞት የመጋለጥ መጠናቸው ምን ያህል እንደቀነሰ ተለክቷል።

በጥናቱ መሠረት፤ ከ1.5 ኪሎ ግራም በታች የሆኑ ልጆች የመሞት ዕድላቸው 52 በመቶ ዝቅ ብሏል።

የልጆችን ክብደት ማስተካከል ይቻላል?

ማሳጁ ቬጋስ የተባለ ነርቭን እንደሚያስተካክል ጥናቶች ያመለክታሉ።

ይህ ነርቭ አንጎልን ከሆድ ጋር የሚያስተሳስር ነው። ነርቩ ሲስተካከል ምግብ በተሻለ ሁኔታ ይፈጫል። የተመጣጠነ ምግብ ይዘትን ሰውነት አሟጦ እንዲወስድም ያግዛል።

ነርቩ ማሳጅ ሲደረግ የልጆች የሰውነት ክብደት እንዲስተካከል ይረዳል። በተለይም ጨቅላ ልጆች ሆዳቸው ማሳጅ ሲደረግ ከሕመም ያገግማሉ።

በተጨማሪም ሆስፒታል ውስጥ ለወራት ብቻቸውን የሚቆዩ ልጆች ከሚፈጠርባቸው ጭንቀት የሚገላግል ሰው።

የልጆች ሕክምና እና ሥነ ልቦና ባለሙያዋ ቲፍኒ ፊልድ እንደሚሉት፤ ወላጆች ልጆች እንደወለዱ ማሳጅ እንዲያደርጓቸው ይመከራል።

በተለያዩ አገሮች ለልጆች የሚሰጥ ማሳጅን ያጠናችው ቲፍኒ፤ ልጆች ማሳጅ ሲደረጉ በስሱ መሆን አለበት ትላለች።

በጣም ስስ የሆነ ማሳጅ ውጤታማ ከመሆን ይልቅ ልጆችን አዝናንቶ የሚያልፍ ነው። ልጆችን በጣም መጫንም ጉዳት ያስከትላል።

ስለዚህ ባለሙያዋ በተመጣጠነ መንገድ ልጆችን ማሳጅ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ታስረዳለች።

የጎንዮሽ ጉዳት አለው?

የአእምሮ እና እድገት ባለሙያው ጌሪ፤ ጨቅላ ልጆችን በጣም ተጭኖ ማሳጅ ማድረግ ስስ ቆዳቸውን እንደሚጎዳው ይናገራል።

ለማሳጅ የሚውለው ዘይት በጥንቃቄ መመረጥ አለበት።

በደቡብ ሕንድ እአአ በ2013 አካባቢ በ194 ልጆች ላይ የተሠራ ጥናት ማሳጅ መደረግ ያለበት የትኛው የሰውነት ክፍል እንደሆነ ፈትሿል።

ከእነዚህ ልጆች አብዛኞቹ በእናቶቻቸው ነው ማሳጅ የተደረጉት። እናቶቹ የልጆቹን ዓይን እና ጆሮ በዘይት አሽተው ነበር። ይህም የልጆችን ጤና እንደሚጎዳ ባለሙያዎች ደርሰውበታል።

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና ባለሙያው ጎጂ የሆኑ የማሳጅ ልምዶች እንዲቆሙ ይመክራሉ።

"ማሳጁ በትክክለኛው መንገድ ነው መሰጠት ያለበት" ይላሉ።

ተመራጭ የሆኑት ዘይቶች የሱፍ፣ የኮኮናት እና የሰሊጥ ናቸው።

እነዚህ የዘይት ዓይነቶች ከፍተኛ የሊኖሊክ አሲድ ክምችት እንዳላቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ። በዘይቶቹ ያለው ፋቲ አሲድ የቆዳን ሕመም የመከላከል አቅም ያጎለብታል።

ከዚህ በተቃራኒው የሰናፍጭ ዘይት ሰውነት ይለበልባል።

በሕንድ ፑን ከተማ የምትኖረው ፕራንጃሊ ብሆንዴ፤ ልጇ ከተወለደ ጀምሮ ማሳጅ አድርጋዋለች። አሁን ልጇ 14 ወር ሞልቶታል።

ፕራንጃሊ በየቀኑ ሁለት ጊዜ ልጇን ማሳጅ ስታድግ እናቷም ያግዟታል።

"ልጄን ማሳጅ የማደርገው ዓይኑን እያየሁ ስለሆነ ትስስራችን እንደጠበቀ ይሰማኛል። በየቀኑ ማሳጅ በመደረጉ ምክንያት እንቅልፉና ቆዳውም ተስተካክሏል" ትላለች።

ማሳጅ ለልጆች ፍቱን ፈውስ እንደሚሰጠው ሁሉ ለዕድሜ ባለጸጎችም ይመከራል። ዕድሜ ሲጨምር የሰውነት ቆዳ ለአደጋ ስሱ እየሆነ ስለሚሄድ በማሳጅ ማጠንከር ይቻላል።

ማሳጅ ለእናቶች ምን ይጠቅማል?

ረኑ ከቤተሰቦቿ የወረሰችው ልጅን ማሳጅ የማድረግ ባህል ብቻ አይደለም። ወላድ እናትም ማሳጅ እንደሚያስፈልጋት ተምራለች።

በ40 ዓመቷ የመጀመሪያ ልጇን የወለደችው ረኑ እንደምትለው፤ ልጇ ከማሳጅ በኋላ ለአራት ሰዓት ያለማቋረጥ ሰላማዊ እንቅልፍ ትተኛለች።

ልጅቷ ያለማቋረጥ መተኛቷ እናትም እረፍት እንድታገኝ ረድቷታል።

"እሷ ስትተኛ እኔም አርፋለሁ። ማሳጅ ለጤናማ የልጅ አስተዳደግ ጠቃሚ መሆኑን ተረድቻለሁ" ትላለች።

ማሳሰቢያ፡ ጨቅላ ልጆችን ያለ ሐኪም ምክር ማሳጅ ማድረግ አይመከርም። ያለ ሐኪም ትዕዛዝ እና መመሪያ ልጆችን ማሳጅ ለማደረግ መሞከር ልጆቹን ለጉዳት ያጋልጣል። እናም ልጅዎች ማሰጅ ለማድረግ ከመወሰንዎ በፊት ሐኪም ያማክሩ።