ሁለት የኡጋንዳ ወታደሮች ሶማሊያ ውስጥ ሞት ተፈረደባቸው

ሶማሊያ ውስጥ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የተሰማራው የአሚሶም ጦር አባል የሆኑ አምስት የኡጋንዳ ወታደሮች ሰባት ሲቪሎችን በመግደል ባለፈው ሐሃምሌ ወር ጥፋተኛ ከተባሉ በኋላ ሁለቱ ሞት ተፈረደባቸው።

ቀሪ ሦስቱ ወታደሮች ደግሞ የ39 ዓመት እስራት የበየነባቸው ሲሆን ለኡጋንዳ መንግሥት ተላልፈው እንደሚሰጡና ፍርዳቸውን በአገራቸው እንደሚጨርሱ ታውቋል።

ሰባቱ ሲቪሎች ጎልዌዩን በተባለው አካባቢ በአልሸባብ እና በአሚሶም ወታደሮች መካከል በነበረ ውጊያ ወቅት ከሕግ ውጪ መገደላቸውን የአፍሪካ ሕብረት ገልጿል። የአሚሶም ጦር በሶማሊያ ከተሰማራ 14 ዓመታትን አስቆጥሯል።

አሚሶም በሶማሊያ ካለው 20 ሺህ ጦር ውስጥ አንድ ሦስተኛው ገደማ የሚሆኑት ከኡጋንዳ የመጡ ሲሆኑ ይህም ኡጋንዳን ከቀጠናው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር ያዋጣች አገር ያደርጋታል።

ቅዳሜ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ የተቀመጠው ወታደራዊ ፍርድ ቤት የአፍሪካ ሕብረት በሶማሊያ ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማስፋት እቅድ እንዳለው ይፋ ካደረገ ከአንድ ወር በኋላ ነው።

ይህ ዕቅድም የሶማሊያን መንግሥት ብሎም የተባበሩት መንግሥታትን ውሳኔ እየጠበቀ ይገኛል።

"በሶማሊያ ያለን ተልዕኮ አል-ሸባብን ጨምሮ ሌሎች የታጠቁ ቡድኖችን አቅም ማዳከም ነው። ይህንን ስናደርግ ግን ሲቪሎችን የመጠበቅ ግዴታ አለብን" ሲሉ በአሚሶም የኡጋንዳ ጦር አዛዥ ብርጋዲየር ጄነራል ዶን ናባሳ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ድምጽ እንደዘገበው የሟች ሲቪሎች ቤተሰቦች የኡጋንዳ መንግሥት፣ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ባዘጋጀው ችሎት ላይ ታድመው ነበር።

"በፍርድ ቤቱ ውሳኔ በጣም ደስተኛ ነን፤ ለሟች ቤተሰቦችም ካሳ እንደሚሰጣቸውም ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉ በሐዘን ላይ የሚገኙት ቤተሰበች ወኪል የሆኑት ሁሴን ኦስማን ተናግረዋል።

ሁሴን አክለውም አንድ ሐዘንተኛ እንዲሁም ስድስት የኡጋንዳ ወታደሮች በችሎቱ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።