ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተመድ እና የኢሰመኮ ሪፖርት ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን እንደ አማራጭ አቀረበ
በሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ሲካሄድ የነበረው የምርመራ ውጤት ይፋ ሆነ።
ዛሬ ይፋ የሆነው እና ለወራት በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የጋራ የምርመራ ቡድን የተካሄደው ምርመራ ውጤት ሪፖርት በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት የተለያዩ በደሎችን መፈጸማቸውንና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠይቋል።
በዚህም መሠረት ሪፖርቱ አገራቱ ለተፈጸሙ በመብት ጥሰቶች እና በደሎች ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ካልቻሉ ወይም ካልፈለጉ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲታይ ሊደረግ የሚችልበትን ዕድል አመልክቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጥምር የምርመራ ሪፖርትን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ሪፖርቱን በበጎ ጎኑ እንደሚመለከተው ነገር ግን ልዩነቶችና ቅሬታዎች እንዳሉት አመለክቷል።
በሪፖርቱ ግኝት መሠረትም በመንግሥት በኩል ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች ለመፈጸም ፈቃደኛ መሆኑንና አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
በሪፖርቱ ጦርነቱ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያስከተለውን አስከፊ ተጽእኖ የተፈተሸ ሲሆን ይህም ተከታታይ የመብት ጥሰቶችና ግፎች መፈጸማቸውን አመልከቷል። ከእነዚህም ውስጥ ከሕግ ውጪ ግድያና ርሸና፣ ማሰቃየት፣ ወሲባዊና ጾታዊ ጥቃቶች፣ በስደተኞች ላይ የተፈጸሙ ግፎች እንዲሁም ሰላማዊ ሰዎችን በኃይል ማፈናቀል ይገኙበታል ብለወል።
ይህ ሪፖርት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ኃይል፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ፋኖ በአንድ ወገን እንዲሁም የትግራይ ልዩ ኃይል፣ የትግራይ ሚሊሻ እና ሌሎች ቡድኖች በሌላ ወገን ሆነው ጦርነት የተካሄደበትን ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም አስከ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትግራይ ክልል ውስጥ በነበረው የአገሪቱ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸማቸውን በመግለጽ የፌደራሉ ሠራዊት እርምጃ እንዲወስድ ማዘዛቸው ይታወሳል።
ከኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በተጨማሪ የአማራ ክልል ኃይሎች እንዲሁም የኤርትራ ጦር በግጭቱ ተሳታፊዎች እንደነበሩ የተዘገበ ሲሆን ህወሓትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን በተመለከተ የመብት ተሟጋቾች ሲወቅሱ ቆይተዋል።
ይህንንም ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ የተካሄደው ምርመራ ውጤት ዛሬ ይፋ ሆኗል።
ምርመራውን ያከናወነው ጥምር ቡድን ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ግጭት ውስጥ የተሳተፉ ሁሉም አካላት በተለያየ ደረጃ የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶችን፣ የሰብአዊ እርዳታ እና የስደተኞች ሕግን፣ አንዳንዶቹም የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ሊባሉ የሚችሉ ጥሰቶችን መፈጸማቸውን በምክንያታዊ ደረጃ እንደሚታመን ገልጿል።
በሲቪል የፍትህ አሰጣጥ አማራጮች ትግበራ ወቅት እነዚህን ሰብአዊ መብት ጥሰቶች በዋናነት የማረም ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ እና በአጥፊዎች ላይ የወንጀል ክስ በመመስረት፣ የዲሲፕሊን እርምጃዎችን በመውሰድ እንዲሁም አስተዳደራዊ ምርመራዎችን በማካሄድ ስልታዊ ጥቃቶችን እንዲለይ በሪፖርቱ ምክረ ሃሳብ ላይ ተቀምጧል።
የወታደራዊ የፍትህ ሥርዓት የወታደራዊ ፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤቶችን እና የመከላከያ ካውንስልን የያዘ ሲሆን ይህንን በመጠቀም በብሔራዊ አማራጮች ፍትሕን መስጠት በሪፖርቱ የተካተተው ሌላው አማራጭ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከሦስት ዓመታት በፊት ያቋቋመው የእርቀ ሰላም ኮሚሽንን በመጠቀም የሚሰጥ ፍትህ ሌላው በአገር ውስጥ የፍትህ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ በሪፖርቱ የተቀመጠ ምክር ነው።
ከዚያ በፊት ግን በአገራቱ ውስጥ ያሉ የፍትህ አማራጮች የተጠቀሱ ሲሆን በዚህም ሲቪል እና ወታደራዊ የፍትሕ ሥርዓቱ፤ ብሎም የእርቀ-ሰላም ኮሚሽንን በመጠቀም በጦርነቱ ወቅት ለተፈጸሙ ጥፋቶች የእርምት ተግባራት ሊሰጡ እንደሚገባ ሪፖርቱ አስቀምጧል።
በሁሉም ወገኖች በኩል ለተፈጸሙ በደሎች ተጠያቂነት እንዲኖር ጥሪ ያቀረበው ሪፖርቱ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አጥፊዎችን ለፍርድ ካላቀረቡ ጉዳዩ ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንደ አንድ አማራጭ ጠቅሷል።
ዓለም አቀፍ የሕግ ሥርዓቶችን በመጠቀም ፍትሕ የሚሰጥባቸውን ሁለት አማራጮች ያስቀመጠው ይህ ሪፖርት የመጀመሪው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት አጥፊዎችን ለፍርድ ካላቀረቡ ጉዳዩ እንዴት ወደ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ሊያመራ እንደሚችል አብራርቷል።
ለዚህም የሮም ስምምነት ተብሎ የሚጠራው እና እ.ኤ.አ በ1998 በጣሊያን ሮማ የተፈረመው ስምምነት የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን ያቋቋመ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያም ሆነች ኤርትራ የዚህ ስምምነት ፈራሚ አገራት ዝርዝር ውስጥ የሉም።
ሪፖርቱ አንድ አገር ወይም የአገራት ዜጎች በዚህ ችሎት የሚዳኙት አገራቱ የሮም ስምምነትን ካልፈረሙ ፍርድ ቤቱ በተፈጸሙት ወንጀሎች ላይ ስልጣን እንደማይኖረው በማስታወስ፤ ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤቱ የሚመራበት አሰራር መኖሩን አመልክቷል።
"እንዲህ አይነቱ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤቱ የመምራት አካሄድ ተፈጻሚ የሚሆነው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወሳኝ የሆኑ ተጠያቂ ግለሰቦችን ለፈጸሟቸው ከባድ ጥፋቶች ተጠያቂ ለማድረግ ካልቻሉ ወይም ካልፈለጉ ነው" ሲል ሪፖርቱ ያስነብባል።
ሁለተኛው የዓለም አቀፍ የፍትህ አሰጣጥ አማራጭ ሆኖ የቀረበው ደግሞ የጋራ የምርመራ ቡድኑ ጥናት ላይ ተጨማሪ ሥራዎችን የሚሰራ ዓለም አቀፍ የምርመራ ቡድን በማቋቋም "ልዩ ችሎት" በመሰየም ጉዳዩን መዳኘት የሚል ነው።
ይህ ልዩ ችሎት ቅይጥ ልዩ ችሎትን ሊያጠቃልል እንደሚችልም ሪፖርቱ አክሏል። ይህም ማለት ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎችን የያዘ እና በተባባሩት መንግሥታት ብሎም በአገራቱ መንግሥት ስምምነት የሚቋቋም ነው።
የምርመራ ግኝቶቹ ምንድናቸው
የጋራ የምርመራ ቡድኑ በምርመራ ወቅት ያገኛቸውን ግኝቶች ከፋፍሎ አቅርቧል።
ሪፖርቱ በቅድሚያ የዳሰሰው ከህግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎችን እንዲሁም ርሸናዎችን ይመለከታል።
"የጋራ የምርመራ ቡድኑ በጦርነቱ ላይ እየተሳተፉ ባሉ ሁሉም አካላት ከህግ ውጪ የተፈጸሙ ግድያዎችን እንዲሁም ርሸናዎችን መርምሯል። የምርመራ ቡድኑ በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረቱ ግድያዎች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ደርሶታል። ይህ በተለይም ወጣት ወንዶች ላይ ያነጣጠረ ነው" ሲል ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
ለዚህም በምሳሌነት ከቀረቡት ክስተቶች መካካል በማይካድራ ከተማ "ሳምረ"' ተብሎ በሚታወቅ ቡድን የተፈጸመ ጥቃት ይገኝበታል።
ምንም እንኳን ቁጥሩን እርግጠኛ ለመሆን ባይቻልም ከ200 በላይ ሰዎች በዚህ ጥቃት ተገድለው በጅምላ መቃብሮች መቀበራቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል።
የመከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ልዩ ኃይል ከተማውን በተቆጣጠሩባቸው ቀጣይ ቀናትም የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የማይካድራ ከተማ ነዋሪዎች ላይ የበቀል ግድያዎች መፈጸማቸውን እና የፋኖ ሚሊሺያዎችም በግድያው መሳተፋቸውን ቡድኑ መረዳቱን ገልጿል።
በተጨማሪም በአክሱም ከተማ የኤርትራ ሠራዊት አባላት ከ100 በላይ ሲቪሎችን መግደላቸውን ብሎም በወቅቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ግድያዎቹ ሲፈጸሙ ጣልቃ ሳይገቡ መቅረታቸውን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
እንዲሁም በቦራ አምደውሃ፣ በቦራ ጫማላ እና ማኢ ሊሃም ከተሞች ከ70 በላይ ሲቪሎች በመከላከያ ሠራዊት መገደላቸውን አክሏል።
እነዚህን እና ሌሎች የግድያ ማስረጃዎችን በመያዝ የሕግ ትንታኔ የሰጠው የምርመራ ቡድኑ በዚህ ጦርነት ውስጥ "የጦር ወንጀሎች" ተፈጽመው ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።
ሌላው በዚህ ጦርነት ተፈጽሟል ተብሎ በሪፖርቱ የተካተተው የማቅይት ተግባራት ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ያወጡትን ሪፖርት በተለመከተ መግለጫ አውጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱ ተቋማት መሪዎችና ሠራተኞች ሙያዊ በሆነ ተአማኒ መንገድ ሥራቸውን በመከወናቸው ምስጋን አቅርበው ነገር ግን ያልተቀብልናቸው የምርመራ ውጤቶች አሉ ብለዋል።
ምንም እንኳ የማንቀበላቸው የሪፖርቱ ክፍሎች ቢኖሩም ተጠቂዎች እንዲካሱ፣ ተጠያቂነት እንዲሰፍን አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን ብለዋል።
"ሪፖርቱ ግጭቱ ከተነሳ ጀምሮ የዕለተ 'ተለት ኑሯቸውን እየገፉ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የደረሰባቸውን አስከፊ ስቃይ ያሳየ ነው" ይላል የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ።
"በግጭት ስም ክብራቸውና ሰብዓዊ መብታቸው የተጣሰ ሰዎች ታሪክ ልብ ሰባሪ ነው።"
ምንም እንኳ መንግሥት ያለውን ስጋት ለጥምር የምርመራ ቡድኑ ቢያቀርብም ምርመራው አንዳንድ መሠረት የሌላቸው ጥሰቶችን መንግሥት እንደፈጸመው አድርጎ ማቅረቡ ተገቢ አይደለም ብሏል።
"ጥምር ምርመራው በግልጽ የዘር ጭፍጨፋ [ጄኖሳይድ] እንዳልተካሄደ አቅርቧል፤ ወቀሳው ማስረጃ እንደሌለውም አሳይቷል። አልፎም የኢትዮጵያ መንግሥት 'ረሃብን እንደ መሣሪያ' እየተጠቀመ ነው መባሉ መሠረተ ቢስ ነው ብሏል።"
መግለጫው አክሎ "የምርመራው ውጤት መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ሆን ብሎ የሰብዓዊ መብት እርዳታ እንዳያገኝ አድርጓል ስለመባሉ በቂ ማስረጃ አላገኘም" ይላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው ያሰፉሩት ባለሁለት ገጽ መግለጫ "እነዚህ ሲቀርቡብን የነበሩ ወቀሳዎች ሐሰት መሆናቸውን ብናውቅም ጠላቶቻችን ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ሲያታልሉ ቆይተዋል" ብለዋል።
ነገር ግን "እነዚህ የሐሰት መረጃዎች እንደ እውነት ተቆጥረው በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መነገራቸው አሳዛኝ ነው" ብለዋል።
ቢሆንም አሁን እነዚህ "የሐሰት መረጃዎች" አሁን በተከፈተው የፀረ ሐሰተኛ መረጃ ዘመቻ ምክንያት እየተጋለጠ ነው ይላል መግለጫው።
በብዙ መንገድ የጥምር ምርመራው ውጤት ከእኛ ምርመራ ጋር ተመሳሳይ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
"ሪፖርቱ እንደሚጠቁመው ህወሓት ግጭቱን ከመጫር አልፎ እጅግ ሰቅጣጭ የሆኑ በደሎችን ፈፅሟል። ነገር ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን አይቶ እንዳላየ አልፏል።"
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርቱ በፈረንጆቹ እስከ ሰኔ 2021 ብቻ ባለው ጊዜ በትግራይ ክልል የተፈፀመውን ያካለለ እንደሆነና በአፋርና በአማራ ክልል "ህወሓት ፈፅሞታል" ያሏቸውን ጥሰቶች እንዳልተካተቱበት ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት ጦር ሠራዊት አባላት ፈፀሟቸው የተባሉን ጥሰቶች በምርመራው መካተታቸው መልካም ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት እያካሄደ ያለውን ምርመራ እንደሚገፋበትና አስፈላጊ እርምጃዎችን እንደሚወስድም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
ለዚህ መሳካት ከፍትህ፣ ሰላም፣ መካላከያ፣ ማኅበራዊ ጉዳዮችና ሴቶች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣ ግብረ ኃይል እያቋቋሙ እንደሆነም አመልክተዋል።