ኢትዮጵያ ከውጭ በሚገባ ስንዴ ላይ ጥርጣሬ ያላት ለምንድነው?

    • ፀሐፊ, በፒተር ምዋይ
    • የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ሪያሊቲ ቼክ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሽታን ጨምሮ በአገሪቱ የሚከሰቱ አብዛኛው የአገሪቱ ችግሮች ምክንያታቸው በእርዳታ ከሚመጣ ስንዴ የመነጩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ስንዴ የሚባል ነገር ኢትዮጵያ እንዳይገባ ካደረግን ሰባ ፐርሰንት የኢትዮጵያ ችግር ይራገፋል። የኢትዮጵያ ችግር የእርዳታ ስንዴ ነው።" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም "ከእርዳታ ስንዴ ጋር በሽታ ይመጣል። ከእርዳታ ስንዴ ጋር ብዙ መዘዝ ይመጣል እሱን ካስቀረን አብዛኛው ችግር ይቀረፋል ማለት ነው።" በማለት ተናግረዋል።

ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ስንዴ ከበሽታዎች እና ሌሎች የኢትዮጵያ ተግዳሮቶች ጋር ማያያዛቸው ትክክል ናቸው?

የኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው የስንዴ ላይ ጥገኝነት

ስንዴ በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ዋና ሰብል ሆኖ አያውቅም፤ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም በከተሞች ዘንድ ተወዳጅነት እያገኘ መጥቷል።

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ ስንዴ አምራች ብትሆንም ምርቱ ካለው ፍላጎት ጋር ሲነፃፃር መመጣጠን አልቻለም።

አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ሚሊዮኖች የምግብ እርዳታ የሚሹባት ሲሆን፣ የምግብ እጥረትና ድርቅንም እየተጋፈጠች ትገኛለች።

በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን እጥረት ለመሙላት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አንድ አራተኛውን ስንዴ ከውጭ እያስመጣች ሲሆን ከዚህም ሩብ ያህሉ ደግሞ በእርዳታ የሚገባ ነው።

አብዛኛውም ስንዴ ደግሞ የሚመጣው ከአሜሪካ ነው።

ከውጭ የሚገባ ስንዴ በሽታ ሊያመጣ ይችላል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኦሮሚያ ክልል አርሶ አደሮችን ባነጋገሩበት ወቅት ከውጭ በሚገባ ስንዴ አማካኝነት በሽታዎች እየመጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ላሉ አርሶ አደሮች በከፍተኛ ሁኔታ ከሚፈትኗቸው የስንዴ በሽታዎች መካከል አንዱ ነፋስ ተሽክሞ የሚያመጣው ፈንገስ ወይንም የስንዴ ዋግ (ሻጋታ) ነው።

ለምሳሌም ያህል በአውሮፓውያኑ 2010 የተከሰተው ወረርሽኝ 30 በመቶ የሚሆነውን የእርሻ መሬት የጎዳ ሲሆን ከ15 በመቶ በላይም ምርቱን እንዲቀንስ አድርጎታል።

የስንዴ ዋግ (ሻጋታ) በሽታን ለመቆጣጠር በጣም ውጤታማው ዘዴ በሸታን መቋቋም የሚችሉ የስንዴ ዝርያዎችን ማራባት ቢሆንም፣ አዳዲስ የፈንገስ ዝርያዎች ግን ሁልጊዜም ስጋት እንደደቀኑ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2013ም እንዲሁ፣ አዲስ የዋግ ዝርያ ከዚህ ቀደም ዲጋሉ በመባል የሚታወቀውና በሽታ ተቋቋሚ የሆነውን የስንዴ ዓይነት በማጥቃቱ ሰፊ ኪሳራ አድርሷል።

በአውሮፓውያኑ 2017 የታተመ ጥናት እንደሚያሳየው ይህ ልዩ የፈንገስ ዝርያ፣ ከየመን በአየር አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ ይታመናል። ይኹን እንጂ ከሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ እና የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የመጣ ሊሆንም ይችላል።

በኢንተርናሽናል ሴንተር ፎር አግሪካልቸራል ሪሰርች ኢን ዘ ድራይ ኤሪያስ (አይካርዳ) የስንዴ ምርት ባለሙያ የሆኑት አቶ ውለታው ታደሰ ደጉ፣ በእርግጠኝነት የሰብል በሽታና ተባዮች በዕርዳታ ወይም ከውጭ በሚገቡ ሰብሎች ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ይላሉ ።

ባለሙያው ይህ በተለይ የማቆያ መገልገያዎች ደካማ በሆኑባቸው አገሮች ውስጥ ሊከሰት እንደሚችልም ያብራራሉ።

"በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ እየተስፋፉ ካሉት ተዛማች አረምና ተባዮች መካከል ብዙዎቹ ከውጪ ገብተዋል የሚሉ ቅሬታዎች ነበሩ" ይላሉ።

"ወንዞቻችን እና ሀይቆቻችን፣ የእርሻ መሬቶቻችን እና የግጦሽ መሬቶቻችን በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ባልነበረ ሁኔታ በተዛማች አረም ስጋት ላይ ናቸው።" በማለትም ባለሙያው ያስረዳሉ።

ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ማንኛውም እህል ከበሽታ የጸዳ መሆኑን በጥንቃቄ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች በሽታ የተስፋፋባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

አንዱ ምሳሌም በቅርቡ በእህል ንግድ አማካኝነት ከደቡብ አሜሪካ ወደ ባንግላዴሽ እና ዛምቢያ የተሸጋገረው 'ዊት ብላስት' የተሰኘው በሽታ ነው። ይህ በሽታ የሚተላለፈው በዘር አማካኝነት ነው።

የስንዴ ዋግ በሽታ በዘሩ ከመሸከም ይልቅ በንፋስ የሚተላለፍ ከመሆኑ አንፃር አዳዲስ ዝርያዎች ከቀጠናው ውጭ ሁልጊዜ አይመጡም።

በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ አንዳንዶቹ አዳዲስ የስንዴ ዋግ ዝርያዎች ከሌሎች አካባቢዎች መምጣታቸውን እንደሚያሳይ ሁሉ አንዳንዶቹ ዝርያዎች በጊዜ ተቀያይረው አዲስ ባህርይ እንዳመጡ የሚያሳይ ማስረጃ አለ።

የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ ) ቃል አቀባይ በበኩላቸው ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የአሜሪካ የምግብ እርዳታ ሁሉንም አዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ለማሟላት ጥብቅ የጥራት ቁጥጥር ይደረግበታል" ብለዋል።

እንዲሁም የአካባቢ የምግብ ደህንነት እና የጥራት ደንቦችንም ባከበረ መልኩ ነው ድጋፍ የሚደረገው በማለት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ምን ይላል?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውጭ የሚገባ ስንዴ በሽታን ያመጣል ማለታቸውን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን ቃለ አቀባያቸውን ቢልለኔ ስዩምን በጠየቅንበት ወቅት የሰጡን ምላሽ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ንግግር በአጠቃላይ ከስንዴ ርቆ ጤናማ የሃገር ውስጥ ምርትን መጠቀም ጋር በተያያዘ መናገራቸውን ገልጸዋል።

"ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ የስኳር በሽታ የመሳሰሉት ከፍተኛ ካርቦሃይድሬት ካላቸው ምግቦች ጋር የተቆራኙ ናቸው። ስለዚህ አጠቃላይ መልዕክቱ የራሳችንን የግብርና ምርታማነት በማሳደግ የእርዳታ ጥገኝነትን መቀነስ አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ነው።" ብለዋል።

ቃለ አቀባይዋ የሰጡት ምላሽ ግን መንግሥት ከውጪ ከሚገባው ስንዴ ጋር ብቻ ችግር እንዳለበት እንጂ በአገር ውስጥ የሚመረተው ሰብል ላይ እንዳልሆነ ነው።

የአገሪቱ አጠቃላይ የስንዴ አቅርቦት ሶስት አራተኛው የሚመረተው በአገር ውስጥ ነው።

ቢልለኔ አክለውም ከውጭ በሚገባ የስንዴ ምርት ጥገኝነት ማቆምም ቀጥተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚቆጥብም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከውጭ ለሚገባ ስንዴ ድጎማ በማድረግ ለትላልቅ ዱቄት ፋብሪካዎች የምታቀርብ ሲሆን ፤ እነዚህ ፋብሪካዎች ዱቄቱንም በቁጥጥር ዋጋ ለዳቦ መጋገሪያዎች ይሸጣሉ።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ማቆም ማለት መንግሥት ለእነዚህ የስንዴ ግዢዎች ለመደጎም ገንዘብ አያጠፋም ማለት ነው።

"በእርዳታ ላይ ያለው ጥገኝነት አብዛኛው ኢትዮጵያውያን እንዲሁም አፍሪካውያን ሃብትን በብቃት እንዳይጠቀሙ አግዷል" ይላሉ ቢልለኔ

አክለውም "እንዲሁም ስንዴ ከውጭ ለማስገባት የሚውለው የውጭ ምንዛሪ ወደ ሌሎች የምርት ዘርፎች መግባት ይጀምራል።" በማለት ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ በበለጠ ስንዴ ማምረት ትችላለች?

በኢትዮጵያ አብዛኛው ስንዴ የሚመረተው በአነስተኛ አርሶ አደሮች ነው።

ሆኖም ከመንግሥት በተገኘው መረጃ መሰረት ባለፉት 15 ዓመታት የመካናይዝድ እርሻ ምርት በእጥፍ ጨምሯል።

ይሁን እንጂ በአሁኑናዊው ሁኔታ ምርታማነት ዝቅተኛ ሲሆን እና ምርቱም ካለው ፍላጎት ያነሰ ነው።

በተለምዶ ስንዴ በኢትዮጵያ የሚመረተው በከፍተኛ ( በደጋ )አካባቢዎች ሲሆን ከዝናብም ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው።

በአሁኑ ወቅት ዝቅተኛ (ቆላማ) በሆኑ ስፍራዎች የመስኖ ልማትን በመጠቀም ምርቷን እየጨመረችም ትገኛለች።

ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት 'ኩታ ገጠም' (ክላስተር)ና መካናይዝድ እርሻን በማበረታታትና እንደ ማዳበሪያና ጥራት ያለው ዘር ያሉ ግብአቶችን ድጎማ በማድረግና በማከፋፈል ላይ ይገኛል።

በዚህም አሰራር ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2023 ሙሉ በሙሉ ስንዴ ከውጭ ማስገባትን ለማቆም እየሰራች ነው።

ባለሙያው አቶ ውለታው ታደሰ ይህንንም በተመለከተ "ያልታረሰና በመስኖ ሊለማ የሚችል 500 ሺህ ሄክታር መሬት ስላለን በጣም ተጨባጭ እና ሊደረስበት የሚችል ግብ ነው" ብለዋል ።