የሱዳን መፈንቅለ መንግሥት፡ በወታደራዊው ኃይል ተቃውሞ ሦስት ሰዎች ተገደሉ

በሱዳን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመደገፍና ወታደራዊ ኃይሉን በመቃወም አደባባይ በወጡ ተቃዋሚዎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች በቀጥታ በተኮሱት ጥይትና አስለቃሽ ጭስ ቢያንስ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የሐኪሞች ኮሚቴ አስታወቀ።

ቅዳሜ ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ወደ ሥልጣን እንዲመለሱ በዋና መዲናዋ ካርቱም እና በሌሎች ከተሞች አደባባይ በመውጣት ጠይቀዋል።

የአገሪቷ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የጸጥታ ኃይሎች በቀጥታ በተቃዋሚዎች ላይ ተኩሰዋል መባሉን ሀሰት ነው ብሏል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን ሌሎች ወደ 100 የሚጠጉ ሰዎችም ለጉዳት እንደተዳረጉ ተናግረዋል።

መፈንቅለ መንግሥቱን የመሩት ጀነራል አብደል ፈታህ ቡርሃን የሲቪል አስተዳደሩን የበተኑት በዚህ ሳምንት ነበር።

ጀነራሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ሲሆን "መፈንቅለ መንግሥቱን ያደረኩት በአገሪቷ የእርስ በርስ ጦርነትንና ፖለቲካዊ ሽኩቻን ለማስወገድ ነው" ብለዋል።

መፈንቅለ መንግሥቱ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውግዘትን አስከትሏል።

ወታደራዊ ኃይሉ ሥልጣን መቆጣጠሩን በመቃወም አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች የሱዳንን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ እንዲሁም "ወታደራዊ አገዛዝ አንፈልግም" በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በካርቱም 'የሬዚስታንስ' ኮሚቴ አባል የሆኑት ሻህን አል ሻህፍ "ሰዎች ሰላማዊ ናቸው። ምንም እንኳን ከጸጥታ ኃይሎች ጥይት ቢተኮስባቸውም ተቃውሞው በሰላማዊ መንገድ ይቀጥላል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ጀነራል ቡርሃን ሁሉንም ደጋፊዎቹን እንዳጣ ተረድተናል ሲሉም ሻህን አክለዋል።

" ይህ አንድ ሰው ያካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ነው ። የሚደግፈው ማንም የለም" ብለዋል ሻህን።

ገለልተኛ የሆነው የሱዳን ሴንትራል ሐኪሞች ኮሚቴ በኦምዱርማን በተቃዋሚዎች ላይ በተተኮሰ ጥይት ተመትተው ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።

የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን በተቃዋሚዎች ላይ ጥይት ተተኩሷል መባሉን ሀሰት ነው ያለ ሲሆን የተወሰኑ ተቃዋሚዎች ፖሊስ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል ሲል ከሷል።

በዚህ ሳምንት ብቻ በተቃዋሚዎችና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በነበረ ግጭት ከ10 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

የሱዳን ባለሥልጣናት የኢንተርኔትና ሌሎች የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶችን ያቋረጡ ሲሆን የእንቅስቃሴ ገደብም ጥለዋል።

እአአ 2019 አገሪቷን ለረዥም ዓመታት የመሩት ኦማር ሀሰን አል ባሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ባሳለፍነው ሰኞ መፈንቅለ መንግሥቱ እስከሚካሄድ ድረስ የሲቪልና ወታደራዊ ኃይሎች ሥልጣን በመጋራት ሱዳንን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል።