ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዳን መፈንቅለ መንግሥት፡ ጦሩ ሥልጣን መያዙን ተከትሎ የዓለም ባንክ እርዳታውን አቋረጠ
የሱዳን ጦር በሲቪል መንግሥቱ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄዱን ተከትሎ የዓለም ባንክ ለሱዳን የሚሰጠውን እርዳታ አቁሟል።
ሰኞ ዕለት የፖለቲካ መሪዎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ተቃውሞዎችን እና ዓለም አቀፍ ውግዘቶችን አስከትሏል።
የአፍሪካ ሕብረትም ሱዳንን ከሕብረቱ አባልነት አግዷታል። አሜሪካ ደግሞ 700 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ አግዳለች።
የሱዳን ሲቪል እና ወታደራዊ መሪዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት በሥልጣን ክፍፍል ፍጥጫ ላይ ነበሩ።
እርዳታ መቋረጡ ኢኮኖሚ ላይ አስከፊ መዘዝ ሊያመጣ ይችላል ተብሏል።
የዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ሕብረት የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ ቡርሃን ሥልጣኑን ለሲቪል መንግሥቱ እንዲመልሱ የበለጠ ጫና ይፈጥራሉ።
የሥልጣን መጋራቱን ስምምነት የመሩት ጄኔራል ቡርሃን መፈንቅለ መንግሥቱ ያስፈለገው "የእርስ በርስ ጦርነት" ለማስቀረት ነው ብለዋል። አሁንም ሱዳን ወደ ዲሞክራሲ እና ወደ 2023 ምርጫ እየገሰገሰች ነው ሲሉ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ምክንያታቸው እና በድንገት የወሰዱት ሥልጣን በብዙዎች ውድቅ ተደርጓል።
የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ "በሱዳን ያሉ የቅርብ ጊዜ ክስተቶች በጣም ያሳስቡኛል። ይህ በአገሪቱ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የማገገም ሂደት እና እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ብዬ እሰጋለሁ" ብለዋል በመግለጫቸው።
በመጋቢት ወር ሱዳን ውዝፍ ዕዳዋን ካጸዳች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓለም ባንክ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ድጋፍ ማግኘት ችላለች። አገሪቱ ለዓመታት በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከገባች በኋላ የተወሰነ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ነው ሲሉ ማልፓስ በወቅቱ ገልጸዋል።
የዓለም ባንክ የሱዳንን ግብርና፣ ትራንስፖርት፣ ጤና እና ትምህርት ለመደገፍ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ያህል ዕርዳታ መስጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ተናግረዋል።
ባለፈው ወር ለዓለም ባንክ ባደረጉት ንግግር ኢኮኖሚው የመረጋጋት ምልክቶችን እያሳየ መሆኑን ጠቁመው በገንዘብ ድጋፉ የተደረጉ ለውጦች "ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል" ብለዋል። አሁን ይህ ሁሉ እንደገና አደጋ ላይ ነው።
የአፍሪካ ሕብረት በትዊተር ገጹ እንዳስታወቀው ከሰኞ ጀምሮ በእስር ላይ የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ መፈታታቸውን በደስታ ቢቀበልም የሱዳን የሲቪል መንግሥት ወደነበረበት እስኪመለስ ድረስ ከሕብረቱ ታግዳ እንደምትቀጥል አስታውቋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሱዳን የሲቪል መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም ሳዲቅ አል-ማህዲ ጋር መነጋገራቸውንና ወደ "ሲቪል መር ዲሞክራሲ ሽግግር" የሚደረገውን ጉዞ እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል።
ረቡዕ ረፋድ ላይ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት ስድስት የሱዳን አምባሳደሮች በወታደራዊው ኃይል ከሥልጣን መነሳታቸው ተነግሯል።
ከሥራቸው የታገዱት የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ቻይና አምባሳደሮች ሲሆኑ ሁሉም የጦሩን ድርጊት አውግዘዋል።
በሱዳን የጎዳና ላይ ተቃውሞው ለሦስተኛ ቀን የቀጠለ ሲሆን ወታደሮች በሕዝቡ ላይ ተኩስ ከፍተው በትንሹ 10 ሰዎች ተገድለዋል። ወታደሮች በካርቱም ቤት ለቤት በመዞር የተቃውሞ አስተባባሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ተዘግቧል።
ሐኪሞች እና የነዳጅ ሠራተኞችን የወከሉ የሠራተኛ ማሕበራት ተቃውሞውን እየተቀላቀሉ ሲሆን የሱዳን የባንክ ማሕበር ሠራተኞችም ተመሳሳይ እርምጃ እየወሰዱ ነው።
የማሕበሩ ቃል አቀባይ አብዱል ራሺድ ከሊፋ "ማንኛውንም ወታደራዊ እርምጃ እና ማንኛውንም ዓይነት አምባገነንነት በፅኑ እንቃወማለን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለረዥም ጊዜ አገሪቱን የመሩት ኦማር አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በሲቪል እና በወታደራዊ መሪዎች መካከል ስምምነት እአአ በ2019 ተፈርሟል። የሥልጣን ክፍፍሉ ሱዳንን ወደ ዲሞክራሲ ለመምራት ታስቦ የተነደፈ ቢሆንም በርካታ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ተደርገዋል። ከአንድ ወር በፊትም በተመሳሳይ መፈንቅለ መንግሥት ተሞክሯል።