ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር እስክትመለስ ድረስ ከአፍሪካ ሕብረት አባልነት ታገደች
የአፍሪካ ሕብረት ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር እስክትመለስ ድረስ በየትኛውም የሕብረቱ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዳትሳተፍ ማገዱን አስታወቀ።
ሕብረቱ ሰኞ ዕለት በሱዳን የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲል ያወገዘ ሲሆን በቁጥጥር ሥር የሚገኙ የሲቪል መሪዎች በአፋጣኝ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርቧል።
የአፍሪካ ሕብረት በአገሪቷ የተከሰተውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ለመፍታት የወታደራዊ እና ሲቪል መሪዎች ጋር ለማነጋገር ተወካዮቹን ወደ ሱዳን መላኩን ገልጿል።
የሱዳን ጦር በአገሪቷ የሲቪል አስተዳደርን እንዲመልስ ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጫና እየተደረገበት ነው።
የዓለም ባንክ ለሱዳን የሚሰጠውን ድጋፍ ሰርዟል።
አሜሪካም ጦሩ የሲቪል አስተዳደሩን ወደ ሥልጣን እንዲመልስ ጫና ለመፍጠር ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ እያሰበች እንደሆነ አስታውቃለች። ቀደም ብሎ አሜሪካ በመፈንቅለ መንግሥቱ ምክንያት ለሱዳን ለመስጠት አቅዳ የነበረውን የ700 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አግዳለች።
ወታደራዊ መንግሥቱ ሥልጣን መቆጣጠሩን በመቃወም በሱዳን ካርቱም እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ ለሦስተኛ ቀን ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።
በተቃውሞው የሰዎች ሕይወት የጠፋ ሲሆን በርካታ ተቃዋሚዎችም ለጉዳት መዳረጋቸው ተዘግቧል።
ሐኪሞችንና የነዳጅ ተቋማት ሠራተኞችን ያካተተው የባለሙያዎች ማኅበራትም ተቃውሞውን መቀላቀላቸውን አስታውቀዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሥልጣን የተወገዱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተከትሎ በስልክ አነጋግረዋቸዋል።
ሰኞ ዕለት በሱዳን የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በቁም እስር ላይ ነበሩ።
ከሥልጣን የተወገዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ቤት የቆዩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።
ጄኔራሉ "ለራሳቸው ደኅንነት" ሲባል ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቤታቸው አስጠልለዋቸው እንደነበር ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አንቶኒ ብሊንከን በሱዳን በቁም እስር ላይ የሚገኙ የሲቪል መሪዎች እንዲፈቱ በድጋሚ ወታደራዊ ኃይሉን አሳስበዋል።
በአውሮፓውያኑ 2019 ለአስርት ዓመታት ሱዳንን የገዙት ኦማር አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በሲቪል መሪዎች እና በወታደራዊ አቻዎቻቸው መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል።
በሲቪል እና በወታደራዊ መሪዎች መካከል የተደረገው የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት ሱዳንን ወደ ዲሞክራሲ ለመምራት የተነደፈ ቢሆንም ካለፈው አንድ ወር በፊት የተደረጉ በርካታ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ግን በተፃራሪው አገሪቷ በተቃራኒው አቅጣጫ እየሄደች እንደሆነ ያመላከተ ነው።
የሥልጣን መጋራት ምክር ቤት መሪ የነበሩት ጄኔራል ቡርሐን ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመሸጋገር ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀው ምርጫው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2023 ሐምሌ ወር ሊካሄድ እንደታቀደ ተናግረዋል።