ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ እየተባባሰ የመጣው የቻይና እና የታይዋን ውጥረት እጅጉን አሳስቦኛል አለች
አሜሪካ በቻይና እና ታይዋን መካከል የተፈጠረው ውጥረት "እጅጉን እንዳሳሰባት" የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቨን ለቢቢሲ ገለጹ።
አማካሪው ይህንን ያሉት ቻይና ለአራት ተከታታይ ቀናት ወደ ታይዋን የአየር ክልል ወታደራዊ ጀቶች መላኳን ተከትሎ ነው።
ታይዋን ራሴን የቻልኩ ግዛት ነኝ ብትልም ቻይና ግን ታይዋንን የምትመለከታት እንደ ተገንጣይ የግዛቷ አካል ነው።
ታይዋን ከግዛቶቿ መካከል ሾልካ ያመለጠች ግዛት እንደሆነች የምታምነው ቻይና፤ ታይዋንን ለመመለስ ኃይል ልትጠቀም ትችላለች።
የአሜሪካው የደኅንነት አማካሪ "በግላችንም ይሁን በሕዝብ ፊት ሰላም የሚያደፈርሱ ድርጊቶችን ከመተቸት ወደኋላ አንልም" ብለዋል።
አሜሪካ ታይዋንን ከቻይና ለመከላከል ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች ወይ? ተብለው የተጠየቁት አማካሪው "ያን የምናደረግበት ቀን እንዳይመጣ ከወዲሁ እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ መልሰዋል።
አሜሪካ ወታደሮቿን ከአፍጋኒስታን ማስወጣቷን ተከትሎ ከዚህ በኋላ ወደ ሌሎች አገራት የፀጥታ ኃይሎቿን መላክ ልታቆም ትችላለች የሚል አንደምታ እንደፈጠረ ጠቅሰው፤ "አፍጋኒስታንን እንደ ማሳያ ወስዶ የአሜሪካን ቆራጥነት ጥያቄ ውስጥ መክተት ትልቅ ስህተት ነው" ብለዋል።
አሜሪካ ፍላጎቷን ሁሌም እንደምታስጠብቅ እና ከወዳጅ አገራት ጎን እንደምትቆም አማካሪው ጄክ ሱሊቨን ተናግረዋል።
ታይዋን ከቻይና የተነጠለችው እአአ በ1949 ኮምኒስቶች ሥልጣን ሲይዙ ነው።
ታይዋን ራሷን የቻለች አገር መሆኗን በይፋ አውጃ ነጻነቷን ለመቀዳጀት የምታደርገው እንቅስቃሴ እየተጧጧፈ ሲመጣ ቻይና ስጋት ገብቷታል።
የታይዋን ፕሬዘዳንት ሳይ ኢንግ-ዌን ይህንን ቀን እውን ያደርጋሉ ብላም ቻይና ትሰጋለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ የቻይናው ፕሬዘዳንት ዢ ዢፒንግ "የታይዋን ስምምነት" የሚባለውን ስምምነት ለመከተል እንደተስማሙ ገልጸዋል።
የደኅንነት አማካሪው ስለ ኢራን ምን አሉ?
የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪው ጄክ ሱሊቨን ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢራን ወደ ኒውክሌር ስምምነት ለመመለስ ጥቂት ሳምንታት እንደሚቀሯት መረጃ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
"ወደ ስምምነቱ የማትመለስ ከሆነ ግን ከወዳጅ አገራት ጋር ተመካክረን የምንወስደውን አቅጣጫ እንወስናለን" ብለዋል።
ኢራን ወደ ኒውክሌር ስምምነት መመለስ ትፈልጋለች? ወይስ ነገሩን በማጓተት ጊዜ ከመግዛት እየሞከረች ነው? የሚለው በቅርቡ የሚታወቅ መሆኑን አማካሪው ገልጸዋል።
"አሜሪካ እንዲህ ላለ ጨዋታ ጊዜ የላትም" ሲሉም የአገራቸውን ቆራጥ አቋም አንጸባርቀዋል።
ኢራን ኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት አሜሪካ 'የማትፈነቅለው ድንጋይ አይኖረም' ብለዋል።
እአአ 2015 ላይ ኢራን፤ ከአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ሩስያ እና ጀርመን ጋር የኒውክሌር ስምምነት ፈርማ ነበር።
ኢራን ይህንን ስምምነት ለመፈረሟ በምላሹ ማዕቀቦች እንዲነሱላት ተወስኖም ነበር።
ነገር ግን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ 2018 ላይ አሜሪካን ከስምምነቱ አስወጥተዋል። ይህ ውሳኔያቸው ስምምነቱ እንዲፈርስ አድርጓል።