ከሰላሳ ዓመታት በኋላ በሶማሊያ ተመልካች በታደመበት ለመጀመሪያ ጊዜ ፊልም ታየ

በሶማሊያ ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ሕዝብ በታደመበት ለመጀመሪያ ጊዜ ፊልም ታየ።

ሞቃዲሾ ውስጥ በሚገኘው የአገሪቱ ብሔራዊ ቲያትር የሲኒማ አዳራሽ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዕይታ የቀረቡት ሁለት አጫጭር ፊልሞች በሶማሊያዊ ዳይሬክተር የተዘጋጁ ናቸው።

በጦርነት ውስጥ ለሦስት አስርት ዓመታት በቆየችው ሶማሊያ ውስጥ እነዚህ ፊልሞች ለሕዝብ ዕይታ የቀረቡት ከባድ የደኅንት ጥበቃ ተደርጎላቸው ነው።

በመዲናዋ የሚገኘው ብሔራዊ ቲያትር ከባድ የእርስ በርስ ጦርነት በሚካሄድበት ዘመን የአጥፍቶ ጠፊ ኢላማ የነበረ ሲሆን የተለያዩ የጦር አበጋዞች መቀመጫ ሆኖ ነበር።

የፊልሙ አዘጋጅ አብዲካዲር አብዲ ዩሱፍ ፊልም መታየት መጀመሩን ተከትሎ "ለሶማሊያ ሕዝብ ታሪካዊ ምሽት ነው" ሲል ገልጾታል።

"ከበርካታ ዓመታት ችግር በኋላ. . . የአገሪቱ ተስፋ እያንሰራራ መሆኑን ያሳያል" ሲል ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ተናግሯል።

"ይህ ለሶማሊያውያን የሙዚቃ ጸሐፊዎች፣ ደራሲያንና የፊልም ዳይሬክተሮች እና ተዋንያኖች ችሎታቸውንና ተሰጥኦአቸውን ለሕዝብ እንዲያቀርቡ መድረክና ዕድልን ይፈጥራል" በማለት የሲኒማ ቤቱ መከፈት የሚያመጣውን ለውጥ ገልጿል።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ቤተ-መንግሥት እና ምክር ቤት በሚገኝበት አረንጓዴው ቀጠና ተብሎ በሚታወቀውና ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት አካባቢ ወደሚገኘው ቲያትር ቤት ፊልም ለመመልከት የመጡ ሰዎች በርካታ የፍተሻ ቦታዎችን ማለፍ ይጠበቅባቸው ነበር።

አሁን ፊልም ለመመልከት አስር ዶላር ያህል የሚያስከፍለው ቲያትር ቤት፤ ከጦርነቱ መቀስቀስ በፊት የተለያዩ የጥበብና ባሕላዊ ትርኢቶች ይቀርቡበት ነበር።

ቲያትር ቤቱ እአአ በ1967 በቻይናውያን መሃንዲሶች ተገንብቶ በወቅቱ የቻይና መሪ ማኦ ዜዶን አማካይነት ለሶማሊያ በስጦታ የተበረከተ ነው። በተከታዮቹ 20 ዓመታት ውስጥም ቲያትር ቤቱ በሶማሊያ የባህል እድገት ውስጥ ጉልህ የሚባል ሚና መጫወቱ ይነገራል።

ከ30 ዓመት በፊት ሶማሊያ መንግሥት አልባ ሆና የእርስ በርስ ጦርነት ሲካሄድ ዋና ከተማዋን ለመቆጣጠር የሚፋለሙ የጦር አበጋዞች ቲያትር ቤቱን መቀመጫቸው አድርገውት ነበር። በዚህም ሳቢያ ከባድ ጉዳት ደርሶበተ ነበር።

ከስምንት ዓመታት በፊት በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ (አሚሶም) አማካይነት ጥገና ተደርጎለት ቢከፈትም በአልሻባብ ጥቃት ተፈጽሞበታል።

የመዝናኛዎች ዝግጅቶችና ፊልሞች የሞራል ንቅዘትን የሚያስከትሉ ናቸው የሚለው እስላማዊው ታጣቂ ቡድን ቲያትር ቤቱ ታድሶ እንደተጠናቀቀ ነበር በቦምብ ያጋየው።