"በየቀኑ ፈገግ ማለቴን አላቆምም"ፔሌ

ስመ ገናናው የእግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ በቅርቡ ቀዶ ሕክምና አድርጎ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የገባ ሲሆን"በጥሩ ሁኔታ እያገገምኩ ነው" ብሏል።

የ80 ዓመቱ ፔሌ በዚህ ወር የአንጀት ዕጢን ለማስወገድ ቀዶ ህክምና የተደረገለት ሲሆን ረቡዕ ዕለት ከፅኑ ህሙማን ክፍል ቢወጣም መልሶ እንደገና ገብቷል።

የሳኦ ፓውሎ አልበርት አንስታይን ሆስፒታል ፔሌ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል መመለሱን በተመለከተ "ለጥንቃቄ ሲባል የተወሰደ እርምጃ ነው" ብሏል።

"ጓደኞቼ፣ አሁን በጥሩ ሁኔታ እያገገምኩ ነው" በማለት ፔሌ በኢንስታግራም ገጹ ላይ አስፍሯል።

"በዛሬው ዕለት ቤተሰቦቼ መጥተው ጎበኙኝ እናም በየቀኑ ፈገግ ማለቴን አላቆምም አልኩ። ከሁላችሁም ላገኘሁት ፍቅር ሁሉ አመሰግናለሁ።" በማለት ተናግሯል።

ምርመራ ሲያደርግ የአንጀት ዕጢ መገኘቱን ተከትሎ ለአንድ ወርም ያህል ህክምና ሲከታተል ቆይቷል።

በብራዚል የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን እንደገለፁት ዕድሜው በመግፋቱ ለቅድመ ጥንቃቄ ሲባል ወደ ፅኑ ህክምና እንደተመለሰም ዘግበዋል።

"ፔሌ ትንሽ ከተረጋጋ በኋላ ወደ ከፊል ፅኑ ህሙማን ክፍል ገብቷል" በማለት ሆስፒታሉ መግለጫ አውጥቷል።

"የልቡም ሁኔታም ሆነ አተነፋፈሰሱም ጥሩ ነው" በማለት ሆስፒታሉ አስታውቋል።

የሆስፒታሉ መግለጫ ከመውጣቱ በፊት ሴት ልጁ በኢንስታግራም ላይ በፃፈችው ፅሁፍ "እየተባለ ያለው አሉባልታ ምን እንደሆነ አላውቅም ነገር ግን በርካቶች መልዕክት እየላኩልኝ ነው" በማለት ተናግራለች።

"በዕድሜ የገፋ ሰው እንዲህ አይነት ቀዶ ጥገና በሚያደርግበት ወቅት እንደ ተለመደው ማገገሚያ አይሆንም። ሁለት እርምጃ ወደ ፊት አንድ እርምጃ ወደ ኋላ ነው። በዕድሜ ለገፋም ሰው የተለመደ ነው" በማለት ተናግሯል።

"ትናንት ትንሽ ደካክሞ ነበር ዛሬ ደግሞ ተሻሽሏል" ብሏል ሆስፒታሉ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የፔሌ ጤና አሳሳቢ ሆኗል።የሦስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ፣ የምንግዜም ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የሚንቆለጳጰሰው ፔሌ ባለፈው ዓመት ወደ ሆስፒታል የተወሰደው በሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ምክንያት ነበር።

የ79 ዓመቱ ፔሌ ከዚህ ቀደም ጭኖቹ ላይ ችግር የነበረበት ሲሆን በዚህም የተነሳ በድጋፍ ለመንቀሳቀስ ተገዶ ነበር። ከቅርብ ጊዜያትም ወዲህም ወደ ህዝብ በቀረበባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆኖ ሲንቀሳቀስ ታይቶ ነበር።

ፔሌ በዓለም ክብረወሰን የተመዘገበለት 1,281 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን በ21 ዓመት የተጫዋችነት ዘመኑ 1,363 ጊዜ በጨዋታ ላይ ተሳትፏል።

እንዲሁም ለብራዚል በተሳተፈባቸው 91 ጨዋታዎች 77 ጎሎችን ያስቆጠረ ምርጥ ተጫዋች ነበር።

የፔሌ የጤንነት ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ሲሆን በ2015 የፕሮስቴት ቀዶ ህክምና አድርጓል። በወቅቱ በተደጋጋሚ ወደ ሆስፒታል የሄደ መሆኑም ይታወሳል።