ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቶክዮ ፓራሊምፒክ፡ "ለኢትዮጵያ አገሬ ክብር መስራቴ ደስ ብሎኛል" አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ
ትዕግስት ገዛኸኝ መንግሥቱ በጃፓን፣ ቶኪዮ እየተካሄደ ባለው የፓራሊምፒክ ውድድር ላይ በአንድ ሺህ አምስት መቶ ሜትር የሩጫ ውድድር ላይ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት ታሪክ አስመዝግባለች።
ይህ የወርቅ ሜዳሊያ በኢትዮጵያ የፓራሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ውስጥ አገሪቱ ያገኘችው የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳልያ ነው። ትዕግስት የቶክዮው ፓራሊምፒክ ሁለተኛ ውድድሯ ነው። ከዚህ ቀደም በቱኒዝያ ሚኒማ ማሟያ ውድድር አድርጋ አሸንፋለች።
ቢቢሲ የወርቅ ሜዳሊያ ካስገኘችው አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
ቢቢሲ፡ እንኳን ደስ ያለሽ! ቶክዮ ላይ ታሪክ ነው የሰራሽው። ምን ተሰማሽ?
በጣም ደስ ብሎኛል! ይህ ነው ብዬ መናገር አልችልም። ምክንያቱም ከሚኒማ ውድድሩ ውጪ በፓራሊምፒክ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ስሳተፍ የመጀመሪያዬ ነው። ለኢትዮጵያ ማለት. . . ለአገሬ ክብር በመስራቴ በጣም ደስ ብሎኛል።
ቢቢሲ ፡ ከኢትዮጵያ ወደ ቶክዮ ስትሄጂ ወርቅ አመጣለሁ ብለሽ አስበሽ ነበር?
ወርቅ አመጣለሁ ብዬ ነው በራሴ ያሰብኩት። ምክንያቱም ማን እንዳለ፣ ምን እንደሆነ፣ እንዴት እንደሆነ ብዙም አላውቅም። ብዙ ተወዳዳሪ ይኑር፣ ጥሩ ተፎካካሪ ይኑር አላውቅም ነበር። እናም እፎካከራለሁ ብዬ ነው የሄድኩት።
ነገር ግን በትክክል በራሴ ውስጤ አስብ የነበረው ወርቅ ለማምጣት ነው። ውድድሩ ሳይታወቅ ይህን አመጣለሁ ብዬ ለሌሎች አልተናገርኩም።
በራሴ ግን ወርቅ አመጣለሁ ብዬ አስቤያለሁ። ወርቅ እንኳን ባላመጣ አሪፍ ውድድር እወዳደራለሁ፤ አሪፍ ውጤት አመጣለሁ ማለትም ቢያንስ ሁለተኛ እንኳን እሆናለሁ ብዬ አስቤያለሁ።
ቢቢሲ፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ፓራሊምፒክ ላይ ወርቅ አምጥታ አታውቅም። ይህን ታውቂ ነበር?
አውቃለሁ። አሰልጣኞችም ሲነግሩን ነበር፤ ዘንድሮ የመጀመሪያው ወርቅ የሚመጣበት ነው ሲሉም ነበር እና ከዚህ በፊት ወርቅ መጥቶ እንደማያውቅ ነግረውኛል፤ ሰምቻለሁ።
ቢቢሲ ፡ ማጣሪያውንም ፍጻሜውንም ስታሸንፊ በብዙ ርቀት ነው ያሸነፍሽው። ሌላ ውድድር ላይ ብሳተፍ ማሸነፍ እችል ነበር ብለሽ ታስቢያለሽ?
በነበረኝ አቋም ሌላ ውድድር ላይ ብሳተፍ አሸንፋለሁ ብዬ አስባለሁ። ለዚህ ውድድር ብዬ ስለተዘጋጀሁ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነበርኩ።
በዚህ ውድድር ሪከርድ ለማሻሻል ባልችልም ወርቅ አመጣለሁ ብየ አስቤያለሁ። ለሪከርዱም ትንሽ ነበር የቀረኝ። ሪከርዱ ስንት እንደሆነ መጀመሪያ አላወቅኩም ነበር። ስሮጥ እየነገሩኝ ነበር፤ ግን አልሰማኋቸውም። ከ
መግባቴ በፊት አስቤበት ስላልገባሁም ይሁን ስላላየሁትም ለሪከርድ አልነበረም የሮጥኩት። ወርቅ እንደማመጣ ግን ወደ ፍጻሜ ውድድሩ ስገባ እርግጠኛ ሆኜ ነበር የገባሁት። ሌላ ውድድር ቢኖርም አሪፍ እሮጣለሁ ብዬ አስባለሁ።
ቢቢሲ፡ እንዳትሮጭ ያደረገሽ ሚኒማ ስላላሟላሽ ነው?
ሰው አልነበረም። ሌላ ርቀት ላይ ያለው ተወዳዳሪ በእኔ በቲ- 13 ዘርፍ ውስጥ አልነበረም። ሚኒማ ላይም አልተሮጠም ይመስለኛል። ሌላ ቦታም ሰው አልነበረም። በዚያ ምክንያት ሌላ ውድድር አልነበረም።
አሁን 5 ሺህ መሮጥ እፈልጋለሁ። ሚኒማ ሲሟላ 5 ሺህ ተሮጦ ቢሆን ኖሮ እዚህም ውድድሩ ይኖር ነበር ሲሉ ነው የሰማሁት፤ እዚያ ላይ ያ አልበረም እና አልተወዳደርንም። በእኔ ፊልድ የለም መሰል . . . የሞከረም ሰው የለም። ግን እርግጠኛ አይደለሁም።
ቢቢሲ ፡ በ1500 ሜትር ቲ-13 ነው የተወዳደርሽው። ቲ-13 ማለት ምን ማለት ነው?
ቲ-13 ማለት ሙሉ ለሙሉ ዓይነ ሥውር ያልሆነ፤ ግን ትንሽ የዕይታ ችግር ያለበት ማለት ነው።
ቢቢሲ፡ እንዴት ነው አትሌቲክስ የጀመርሽው? አርአያሽስ ማነው?
እኔ የተወለድኩት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ኢላኒ ቀርሳ የምትባል አካባቢ ነው። ሩጫ በጣም ነበር የምወደው። ልጅ ሆኜ ትምህርት ቤት እያለን እነ ጥሩነሽ ሮጠው ባንዲራ ለብሰው ሳይ በጣም ነበር ደስ የሚለኝ። በዚያ ምክንያት ትምህርት ቤት እያለሁ ነው ሩጫ የጀመርኩት።
ቢቢሲ፡ ከዚያ የት ክለብ ገባሽ?
እኔ ሩጫ የጀመርኩት 2006 ዓ.ም ላይ ነው̀። ጫጫ የምትባል ትንሽ ከተማ ሄጀ ነው ሩጫ የጀመርኩት። እዚያ ጥቂት ልጆች ተሰባስበው ያሉበት ትንሽ ፕሮጀክት ነበር። መጀመሪያ እዚያ ነበር የገባሁት።
እዚያ እየሰራሁ ቆየሁና 2010 ዓ.ም ላይ ከዚያ ወጥቼ ደብረ ብርሃን ገባሁ። እዚያ እየሰራሁ እያለሁ ነው በ2011 ዓ.ም ላይ ፌደራል ፖሊስ የገባሁት። ክለቤ ፌደራል ፖሊስ ነው።
ቢቢሲ፡ ቶክዮ በተለያዩ ውድድሮች የሚሳተፉ ብዙ አገራት፣ በርካታ አትሌቶችም አሉ። በተደጋጋሚ ሜዳሊያ ያገኙ አትሌቶችም አሉ። እነርሱን አይተሽ ያስቀናሽ ነገር ምንድን ነው?
ሌሎች አገራት በጣም ብዙ ማለትም 20 ወይም 30 ሆነው የመጡ አገራት አሉ። እኛ ከኢትዮጵያ የመጣነው ሦስት ብቻ ነን።
እና የተወዳዳሪ ቁጥር ቢጨምር፣ ድጋፍ ቢኖር እና ሚኒማ ማሟያው ሄዶ ለመወዳደር በዓለም አቀፉ ፓራሊምፒክስ ኮሚቴ ተጨማሪ ሰው ቢሰጠው እና ለኢትዮጵያ ፓራ አትሌቲክስ ተጨማሪ ዕድል ቢሰጥ ኢትዮጵያውያን በጣም ብዙ ማሸነፍ የሚችሉት ውድድር አለ።
ልጆቹ በጣም ጠንካራ ናቸው። የኢትዮጵያ አትሌቶች መሮጥ የሚችሉ ናቸው።
የአሁኑ አልፏል፤ ለወደፊቱ ግን ድጋፍ ተደርጎ የአትሌቶችን ቁጥር መጨመርና ማሻሻል ቢቻል እንዲሁም በአትሌቲክስ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ስፖርት ላይ መሳተፍ ቢቻል አሪፍ ነው። በጣም ጥሩ ውጤት እናመጣለን ብየ አስባለሁ። ከአሁን በኋላ ባለው ላይ እንደዚኣ ቢደረግ መልካም ነው።