ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አፍጋኒስታን፡ ጦርነቱ ስንት ህይወት ቀጥፎ ስንት ገንዘብ ፈጅቶ እዚህ ደረሰ?
ከ20 ዓመታት ወታደራዊ እንቅስቃሴ በኋላ የአሜሪካ እና የሌሎች የውጭ ኃይሎች አፍጋኒስታንን ለቅቀው ሲወጡ ታሊባን በፍጥነት አገሪቱን ተቆጣጥሯል።
ፕሬዝዳንት ባይደን እስከ መስከረም አጋማሽ ድረስ ሁሉም የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን ሙሉ ለሙሉ እንዲወጡ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ አሜሪካ እና የኔቶ አጋሮቿ በአፍጋኒስታን ምን ያህል ወጪ እንዳወጡ እንመለከታለን።
ምን ያህል ኃይሎች ተላኩ?
አሜሪካ ከ9/11 የሽብር ጥቃቶች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ኦሳማ ቢን ላደን እና ሌሎች የአል-ቃይዳ ሰዎችን ይደግፋሉ ያለችው ታሊባንን ከስልጣን ለማውረድ እአአ ጥቅምት 2001 አፍጋኒስታንን ወረረች።
ታሊባንን ለመዋጋት አሜሪካን ቢሊዮን ዶላሮችን ስታፈስ የጦሯ ቁጥርም ጨምሯል። እአአ በ2011 ቁጥሩ 110,000 ገደማ ደርሷል።
አሁን ቁጥሩ ቀንሶ ወደ 650 ገደማ ቀርተዋል። እነዚህም በአፍጋኒስታን ለሚገኙ ዲፕሎማቶች ጥበቃ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል። ታሊባን አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረ በኋላ አሜሪካ ዜጎቿን ለማስወጣት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ዳግም ወደ ካቡል ልካለች።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባላትን ጨምሮ የሌሎች ሃገራትም ጦር በአፍጋኒስታን ይገኙ ነበሩ።
አሜሪካ ትልቁ ተዋጊ ጦር በአፍጋኒስታን ነበራት።
ኔቶ የውጊያ ተልዕኮውን እአአ ታህሳስ 2014 በመደበኛነት አጠናቅቋል። የአፍጋኒስታን ኃይሎችን ለማሰልጠን እና የፀረ-ሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎችን ለመርዳት 13,000 ጠንካራ ኃይሉን እዚያው አቆይቷል።
በአፍጋኒስታን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የግል የደህንነት አባላት አሉ። እንደ አሜሪካ ኮንግረስ ምርምር ከሆነ እስከ 2020 የመጨረሻ ሩብ ዓመት በዚህም ምድብ የሚካተቱ ከ 7,800 በላይ የአሜሪካ ዜጎችን ይገኛሉ።
የአሜሪካ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚሉት ከሆነ ዋሽንግተን አብዛኛዎቹ የግል የደህንነት አባላትም በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ ይለቅቃሉ።
ምን ያህል ገንዘብ ወጪ ተደርጓል?
በአፍጋኒስታን አብዛኛው ወጪ የተደረገው በአሜሪካ ነው።
ከ100,000 በላይ ወታደሮች በሀገሪቱ ውስጥ በነበሩበት እአአ ከ 2010 እስከ 2012 ባለው ጊዜ የጦርነቱ ወጪ በዓመት ወደ 100 ቢሊዮን ዶላር ያህል ማደጉን የአሜሪካ መንግሥት አሃዞች ያሳያሉ።
የአሜሪካ ጦር ትኩረቱን የአፍጋኒስታንን ኃይሎችን ወደ ማሠልጠን ሲያዞር ወጪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል።
እአአ በ2018 ዓመታዊ ወጪው 45 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደነበር አንድ የፔንታጎን ከፍተኛ ባለሥልጣን በዚያው ዓመት ለአሜሪካ ኮንግረስ ተናግረዋል።
በአሜሪካ የመከላከያ መምሪያ መሠረት በአፍጋኒስታን አጠቃላይ ወታደራዊ ወጪ (ከጥቅምት 2001 እስከ መስከረም 2019) 778 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
በተጨማሪም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) እና ከሌሎች የመንግሥት ኤጀንሲዎች ጋር 44 ቢሊዮን ዶላር ለመልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶች ወጪ አድርጓል።
ይህም በኦፊሴላዊ መረጃ ላይ ተመስርቶ በ 2001 እና በ 2019 መካከል ያለውን አጠቃላይ ወጪ ወደ 822 ቢሊዮን ዶላር ያደርሰዋል። አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ጋር ለተያያዙ ሥራዎች ፓኪስታን ውስጥ ያደረገችውን ወጪ አያካትትም።
እአአ በ 2019 በብራውን ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ጥናት መሠረት አሜሪካ 978 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በአፍጋኒስታን እና በፓኪስታን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ወጪ አድርጋለች። (ግምታቸው ለ 2020 የበጀት ዓመት የተመደበውን ገንዘብም ያጠቃልላል)።
ጥናቱ አጠቃላይ ወጪውን ለመገምገም አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሷል። የሂሳብ አያያዝ ዘዴዎች በመንግሥት ቢሮዎች መካከል መለያየቱ እና ዘዴው በየጊዜው መለዋወጡ አጠቃላይ ግምቶች እንዲለያዩ ያደርጋል።
ከአሜሪካ ቀጥሎ በአፍጋኒስታን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች የነበራቸው ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመን በጦርነቱ ወቅት በግምት 30 ቢሊዮን ዶላር እና 19 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርገዋል።
አሜሪካ እና ኔቶ ሁሉንም ወታደሮቻቸውን ቢያስወጡም እስከ 2024 ድረስ ለአፍጋኒስታን ጦር በድምሩ 4 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
በዚህ ዓመት ኔቶ ለአፍጋኒስታን የ72 ሚሊዮን ዶላር መሣሪያና ሌሎች ድጋፎች ልኳል።
ገንዘቡ የት ሄደ?
በአፍጋኒስታን አብዛኛው ገንዘብ የወጣው ለፀረ-ሽብር ተግባራት፣ እንደ ምግብ፣ አልባሳት፣ የህክምና እንክብካቤ፣ ለልዩ ክፍያ እና ጥቅማጥቅሞች ባሉ ወታደራዊ ፍላጎቶች ላይ ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት እአአ ከ2002 ጀምሮ አሜሪካ በአፍጋኒስታን የመልሶ ግንባታ ሥራዎች 143.27 ቢሊዮን ዶላር ያህል ወጪ አድርጋለች።
የአፍጋኒስታን ብሔራዊ ጦርን እና የፖሊስ ኃይልን ጨምሮ የአፍጋኒስታን የፀጥታ ኃይሎችን ለመገንባት ከግማሽ በላይ (88.32 ቢሊዮን ዶላር) የሚሆነው ወጪ ተደርጓል።
ለአስተዳደር እና ለልማት ሥራዎች 36 ቢሊዮን ዶላር ሲመደብ አነስተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ደግሞ ለጸረ-አደንዛዥ ዕጽ እና ለሰብአዊ እርዳታ ተመድቧል።
ከዚህ ገንዘብ ውስጥ የተወሰነው ለዓመታት በማጭበርበር እና በብክነት ጠፍቷል።
በአፍጋኒስታን የመልሶ ግንባታ ጥረቶችን የመከታተል ኃላፊነት ያለበት አንድ ተቋም ለአሜሪካ ኮንግረስ ጥቅምት 2020 ባቀረበው ሪፖርት ከግንቦት 2009 እስከ በታህሳስ 2019 መካከል 19 ቢሊዮን ዶላር ያህል በዚህ መንገድ እንደጠፋ ገምቱን አስቀምጧል።
በሰው ህይወትስ ምን ያህል ተከፈለ?
በታሊባን ላይ የተደረገው ጦርነት እአአ በ 2001 ከተጀመረ ወዲህ ከ 3,500 በላይ የጥምር ኃይሉ አባላት ሞተዋል። ከእነዚህም መካከል ከ 2,300 በላይ የሚሆኑት የአሜሪካ ወታደሮች ናቸው።
ከ450 በላይ የእንግሊዝ ወታደሮች ህይወታቸው አልፏል። 20,660 የአሜሪካ ወታደሮች ደግሞ ቁስለኛ ሆነዋል።
ህይወታቸው ያለፈው የአፍጋኒስታን የፀጥታ ኃይሎች እና የሲቪሎች ብዛት ከላይ ያለውን ቁጥር እጅግ አነስተኛ አድርጎ ያደበዝዘዋል።
እአአ በ 2019 ፕሬዚዳንት ጋኒ መንበሩን ከያዙ ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ ከ 45,000 በላይ የአፍጋኒስታን የጸጥታ ኃይሎች አባላት ተገድለዋል ብለዋል።
እ.ኤ.አ. በ 2019 የብራውን ዩኒቨርሲቲ ምርምር እንዳለው ጦርነቱ ከተጀመረበት ከጥቅምት 2001 ጀምሮ በአፍጋኒስታን በብሔራዊ ጦር እና ፖሊስ የጠፋው ሕይወት ከ 64,100 በላይ እንደሚሆን ገምቷል።