ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የህወሓትና የኦነግ-ሸኔ ጥምረት አዲስና አስደናቂ አይደለም፡ ቢልለኔ ስዩም
የኦነግ ሸኔ እና ህወሓት በይፋ ተጣምረናል ማለታቸው አዲስ ነገር አለመሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክረታሪ ቢልለኔ ስዩም ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የኦነግ ሸኔ እና የአማጺው ቡድን ህወሓት ጥምረት አዲስ ነገር አይደለም ብለዋል።
በኦነግ-ሸኔ እና በህወሓት መካከል ትብብር ስለማድረግ የደረሱትን ስምምነት በተመለከተም ሁኔታ ለመንግሥት አዲስም የሚያስደንቅም አይደለም ያሉት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ፤ ቡድኖቹ ጥምረታቸውን ይፋ ያደረጉበት ጊዜ ሊመረመር ቢገባም መንግሥት ከሁለት ዓመታት በላይ ሸኔ የህወሓትን አፍራሽ ተልዕኮ አስፈጻሚ ነው ሲል መቆየቱን አስታውሰዋል።
ጨምረውም በአገሪቱ ሕግ መሠረት ሁለቱም ቡድኖች ከሦስት ወራት በፊት አሸባሪ ድርጅቶች ተብለው መሰየማቸውን ገልጸው፤ አሁን ይፋ የሆነው ትብብራቸው ቡድኖቹ ለሚያደርጉት በአገሪቱ መረጋጋት ላይ አፍራሽ እንቅስቃሴን ምስክር ነው ብለዋል።
ሸኔ ከኦነግ ተነጥሎ ከመውጣቱ በፊት ህወሓት በርካታ የኦሮሞ ወጣቶችን ሲያሰቃይ፣ ሲገድል፣ ሲያፈናቅልና ደብዛቸውን ሲያጠፋ መቆየቱን የጠቀሱት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ የኦሮሞ ወጣቶችም ይህንን ቡድን ይደግፋሉ ብዬ አላምንም ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎችም መልስ ሰጥተዋል።
የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት
በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ መንግሥት የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ህወሓትን ለመደምሰስ እርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ መቀመጡን ማስታወቁ ይታወሳል።
በመግለጫው የህወሓት እንቅስቃሴን "ለመደምሰስ" እድሜ እና አቅሙ የሚፈቅድለት በሙሉ የፌደራሉንና የክልል ኃይሎችን እንዲቀላቀሉ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ይሁን እንጂ መግለጫው የተናጠል ተኩስ አቁሙ ስለመነሳት አለመነሳቱ በግልጽ ያለው ነገር የለም።
ይህንን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ቢልለኔ፤ "የቀረበው አገራዊ ጥሪ መንግሥት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ህወሓት አገሪቷን ወደ ባሰ አለመረጋጋት እንዳይከታት ለመከላከል የቀረበ ነው" ሲሉ አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
ስለመከላከያ ሠራዊት
መንግሥት አቅሙ የፈቀደና ብቁ የሆነ ዜጋ ሁሉ የአገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአህጉሩ ጠንካራ ሠራዊት እንደሆነ ይታወቃል፤ የዘመቻ ጥሪ መቅረቡ በሠራዊቱ ላይ በቁጥርም ሆነ በጥንካሬ ያጋጠመ ተግዳሮት ይኖር ይሆን ወይ? የሚል ጥያቄ ለፕሬስ ሴክሬታሪዋ ቀርቦላቸው ነበር።
እርሳቸውም ብሔራዊ የዘመቻ ጥሪ ከሠራዊቱ ብቃት ጋር የሚያገኛኘው ነገር የለም። ጥሪው የአገሪቷን ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ የቀረበ ጥሪ ነው ሲሉ መልሰዋል።
"ህወሓት ለጦርነቱ በርካታ ሲቪሎችን እየተጠቀመ ነው። እነዚህ ሲቪሎች ዘረፋ ይፈፅማሉ፤ ንብረት ያወድማሉ፤ ከአማራ ክልል ሴቶችን እንደተደፈሩ ሪፖርት ደርሶናል። በመሆኑም ይህንን ለመከላከል የሁሉንም ሕብረተሰብ ጥረት ይጠይቃል" ብለዋል ፕሬስ ሴክሬታሪዋ።
በሌላ በኩልም እነዚህ ቡድኖች በሌሎች የአገሪቱ ክፍልም ወኪሎች አላቸው፤ በመሆኑም ይህ ብሔራዊ ጥሪ ዜጎችን ለማንቃትና ሁኔታውን እንዲረዱ ለማስቻል ያለመ እንደሆነ ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ተናግረዋል።
አፋር ክልል ስለተፈፀመው ጥቃት
ህወሓት በአፋር ክልል ጋሊኮማ ቀበሌ ተፈናቃይ ሰዎች በተጠለሉበት ጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤት ላይ ጥቃት መፈፀሙን ቢልለኔ ተናግረዋል።
የእርዳታ እህል የተከማቸበት መጋዘንም ወድሟል፤ ይህንንም ተከትሎ ክልሉ በነገው ዕለት የሚጠናቀቅ የሦስት ቀናት ሀዘን አውጇል ብለዋል ፕሬስ ሴክሬታሪዋ።
ህወሓት የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ ወደ አፋርና አማራ ክልል በመግባት የሰዎች ሞገድ ወይም ሲቪል ተዋጊዎችን በመላክ ሰዎችን ገድሏል፣ ዘረፋ አካሂዷል፣ ሴቶችን ደፍሯል ያሉት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ፤ በዚህም ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን አመልክተዋል።
"በአሸባሪው ህወሓት በተፈፀመ ወረራ ባለፉት ሳምንታት በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ ይሁን እንጅ እነዚህ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብን ትኩረት አላገኙም" በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ጨምረውም መንግሥት ይህንን ክፍተት ለመሙላት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ፍጆታዎችን እያቀረበ ሲሆን ተጨማሪ አስፈላጊ እርዳታዎችን ለማቅረብ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ስለታገዱት የእርዳታ ድርጅቶች
ከሁለት ሳምንት በፊት ሦስት ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የአገሪቷን ሕግ በማጣሳቸው ከሥራቸው መታገዳቸው ይታወሳል።
እነዚህ ድርጅቶች ኤም ኤስ ኤፍ ሆላንድ፣ ኖርዌጂያን ሬፊዩጂ ካውንስል እና አልማክቱም ፋውንዴሽን ናቸው። መንግሥት ድርጅቶቹን ያገደበትን ምክንያት በዝርዝር አስቀምጦ ነበር።
ድርጅቶቹ ችግሩን ለመፍታት ከመንግሥት ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነ አስታውቀው ነበር።
ፕሬስ ሴክሬተሪዋ ዛሬ ድርጅቶቹ የተጣለባቸው የሦስት ወር እግድ ይነሳላቸው እንደሆነ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
እርሳቸውም "እነዚህ ድርጅቶች ከሰላም ሚኒስቴር ጋር መነጋገራቸውን አውቃለሁ። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ከመንግሥት አጋር ድርጅቶች ጋር ተነጋግረዋል። ነገር ግን እግዱ የመነሳቱ ነገር በንግግራቸው ላይ የተመሰረተ ነው የሚሆነው" ሲሉ መልሰዋል።