የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተከሳሾች የዕድሜ ልክና የ18 ዓመት ጽኑ አስራት ተፈረደባቸው

ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ጥፋተኛ የተባሉት ተከሳሾች በእድሜ ልክና በ18 ዓመት ጽኑ አስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጠ።
ከአንድ ዓመት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ በተገደለው ታዋቂው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጥፋተኛ የተባለው ጥላሁን ያሚ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተፈረደበት
ጉዳዩን ሲመለከት የነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ችሎት በሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ አንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ ላይ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ሲፈርድ በተጨማሪ ደግሞ ሁለተኛው ተከሳሽ ከበደ ገመቹ ላይ ደግሞ የ18 ዓመት ጽኑ እስራት በይኗል።
ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ነበር የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት የቀረቡለትን ማስረጃዎች መርምሮ አንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ እና ሦስተኛ ተከሳሽ አብዲ ዓለማየሁ በሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጥፋተኛ ናቸው ሲል የወሰነው።
ይህንንም ተከትሎ በድምጻዊው ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ አንደኛ ተከሳሽ ሆኖ የቀረበውና በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባለው ጥላሁን ያሚ በሞት እንዲቀጣ ዐቃቤ ሕግ ጠይቆ ነበር።
ፍርድ ቤቱ ዛሬ ሐምሌ 27/2013 ዓ.ም በነበረው ውሎው በሰጠው ውሳኔ ላይ ከከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረቡትን ቅጣት ማክበጃዎች እንዲሁም ከተከሳሾች በኩል ደግሞ የቅጣት ማቅለያ ሃሳቦችን ተመልክቷል።
በዚህም መሠረት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረባቸውን የተለያዩ የቅጣት ማክበጃ ሃሳቦችን የተቀበለ ሲሆን በተመሳሳይ በተከሳሾች በኩል የቀረቡትን የቅጣት ማቅለያዎችን ተመልክቶ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራትና የ18 ዓመት ጽኑ እስራት ፈርዷል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከግድያው ጋር በተያያዘ ተጠርጥሮ በሦስተኛ ተከሳሽነት በቀረበው አብዲ አለማየሁ ላይ የስድስት ወራት እስራት የፈረደ ሲሆን ነገር ግን ግለሰቡ ከተፈረደበት ጊዜ በላይ በእስር ላይ በመቆየቱ ሌላ ክስ ከሌለበት ከእስር እንዲለቀቅ አዟል።
የዛሬው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከአንድ ዓመት በላይ ሲታይ የቆየውን የሃጫሉ ሁንዴሳ የግድያ ወንጀል ጉዳይን መቆጫ ላይ ያደረሰ ነው። የፍርድ ሂደቱ በመራዘሙ የድምጻዊው ቤተሰቦች ቅሬታቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸው ይታወሳል።
ታዋቂው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በሙዚቃ ሥራዎቹ ከፍተኛ አድናቆትን ያገኘ ሲሆን ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ነበር በጥይት ተመትቶ የተገደለው።
በድምጻዊው ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀል በመላው አገሪቱ ከባድ ድንጋጤንና አለመረጋጋትን የፈጠረ ሲሆን በዚህ ሳቢያ በአዲስ አበባና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በተከሰተው ሁከለት በርካታ ሰዎች መገደላቸውና ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙ ይታወሳል።














