ጄነራል ጻድቃን ገ/ተንሳይን ጨምሮ 74 የጦር መኮንኖች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መሰረተ

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዓርማ

የፎቶው ባለመብት, Attorney General

የምስሉ መግለጫ, የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዓርማ

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሰባ አራት የህወሓት ከፍተኛ የጦር አመራሮች ላይ የፌደራል መንግሥቱን በኃይል ለመጣል በመሞከር የሽብር ወንጀል ክስ መሰረተ።

በትግራይ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የእስር ትዕዛዝ ወጥቶባቸው የነበሩት እነዚህ ወታደራዊ መኮንኖች በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

በዚህ ክስ ውስጥ ከተካተቱት የቀድሞ የአገሪቱ ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መካከል ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ፣ ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤ፣ ሜጀር ጄነራል ዮሃንስ ወ/ጊየርጊስ፣ ብርጋዲየር ጄነራል ምግበ ኃይለ እና ሌሎችም ይገኙባቸዋል።

በሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ስም በተከፈተው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ የተካተቱት ተከሳሾች "የፌዴራል መንግሥትን በኃይል ለመለወጥ በማሰብ በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ከህወሓት አመራሮች ተልዕኮ በመቀበል ጥቃት ለማድረስ የሚችል የትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ አደራጅተዋል" ብሏል።

በዚህም ወታደራዊ ኮማንዱን በመምራት በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ላይ በሚገኙ የሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በፌዴራል የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም በአማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ በተጨማሪም በኤርትራ ላይ ጥቃት አድርሰዋል ብሏል።

በክሱ ውስጥ የተካተቱት 74 ተጠርጣሪዎች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ የተለያዩ አንቀጾችን እና የሽብርን ወንጀል ለመከላከል ለመቆጣጠር በ2012 ዓ.ም የወጣውን አዋጅ ላይ የሰፈረን ድንጋጌ ተላልፈው በመገኘታቸው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሽብር ወንጀል ክስ መመስረቱን አመልክቷል።

ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ ያስረዱልኛል ያላቸውን ከ500 በላይ የሰው ምስክሮችን፣ ከአምሰት ሺህ ገጽ በላይ የሰነድ ማስረጃዎችን እንዲሁም የቴክኒክና የቪዲዮ ማሰረጃዎችን አያይዞ ለፍርድ ቤት ማቀረቡን ገልጿል።

በሰባ አራቱ ወታደራዊ መኮንኖች ላይ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የቀረበውን ክስ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ የፀረ ሽብር ወንጀል ችሎት መዝገብ ተከፍቶ እየተመለከተው መሆኑ ተነግሯል።

ከ74ቱ ተከሳሾች መካከል 20 ዎቹ በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ በቁጥጥር ስር እንደሚገኙና 54ቱ ላይ ደግሞ በሌሉበት ክሱ መመስረቱን ዐቃቤ ሕግ አመልክቷል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባለፈው ሳምንት በደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የመዝገብ ስር በስድሳ ሁለት ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

በዚህ ክስ መዝገብ ውስጥ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፍተኛ አመራሮችና በድርጅቱ ስር የነበሩ የተቋማት ተካተዋል።

በዚህም መሰረት የህወሓት ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር የሆኑት በደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር)፣ ፈትለወርቅ ገብረእግዚያብሔር፣ ጌታቸው ረዳ፣ ዓለም ገብረዋህድ፣ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ 62 ተከሳሾች ያሉበት ሲሆን ከመካከላቸውን በሕግ ቁጥጥር ስር ያሉም ተካተውበታል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ክስ የተመሰረተባቸው የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ውሳኔ በመስጠት ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና የክልልመንግስቱ ካቢኔ አባላት ይገኙበታል።

በተጨማሪም ከተከሰሱት መካከል የኤፈርት ድርጅቶች፣ የግልና የመንግሥት ተቋማት አመራሮች፣ የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን አመራር አባላት፣ በትግራይ በተካሄደው ኢ-ሕገ-መንግስታዊ ምርጫ ላይ ተሳትፎ ያደረጉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊቃነ-መናብርትና የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩ ታዋቂ ግለሰቦች ተካተውበታል።

የቀረበባቸውም ክስ በአድማና ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ምርጫ በማካሄድ በሕገ-መንግሥት የተቋቋመና እውቅና ያለውን የክልል መንግሥት ለወጥ ማድረግ እና የፌደራሉን መንግሥት በኃይል ለመለወጥ የሚችል የትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ የተባለ የጦር ኃይል በማደራጀት በአገር መከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት በማድረስ ነው።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የፌደራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በጥቃቱ ውስጥ እጃቸው አለበት ያለቸውን የቡድኑን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮችን ለመያዝ የሚያስችል የእስር ማዘዣ ማውጣታቸው ይታወሳል።

የፌዴሬሽንም ምክር ቤት የትግራይ ክልል መንግሥትን ሕገ ወጥ በማለት እንዲበተን ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የነበረውን ህወሓት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ብሎ ሰይሞታል።

ለስምንት ወራት ከተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ በኋላ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ክልል ሠራዊቱን ማስወጣቱን ያስታወቀ ሲሆን፤ የህወሓት ኃይሎች በበኩላቸው አብዛኛውን የክልሉን ክፍል መቆጣጠራቸውንና "ሕጋዊው የክልሉ መስተዳደር ወደ ቦታው ተመልሷል" ማለታቸው ይታወሳል።