ዶ/ር ደብረጽዮንንና ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በህወሓት አመራሮች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መሰረተ

የፎቶው ባለመብት, Attorney General
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የመዝገብ ስም በስድሳ ሁለት ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን አስታወቀ።
በዚህ ክስ መዝገብ ውስጥ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፍተኛ አመራሮችና በድርጅቱ ስር የነበሩ የተቋማት ተካተዋል።
በዚህም መሰረት በደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር)፣ ፈትለወርቅ ገብረእግዚያብሔር፣ ጌታቸው ረዳ፣ ዓለም ገብረዋህድ፣ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ 62 ተከሳሾች ያሉበት ሲሆን ከመካከላቸውን በሕግ ቁጥጥር ስር ያሉም ተካተውበታል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ክስ የተመሰረተባቸው የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ውሳኔ በመስጠት ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና የክልልመንግስቱ ካቢኔ አባላት ይገኙበታል።
በተጨማሪም "በተፈጸመው ጥቃት ላይ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው የተባሉ የኤፈርት ድርጅቶች፣ የግልና የመንግሥት ተቋማት አመራሮች፣ የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን አመራር አባላት፣ በትግራይ በተካሄደው ኢ-ሕገ-መንግስታዊ ምርጫ ላይ ተሳትፎ ያደረጉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሊቃነ-መናብርትና የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩ ታዋቂ ግለሰቦች" ክሱ ውስጥ ተካተዋል ብሏል ዐቃቤ ሕግ።
የቀረበው ክስ በሁለት የወንጀል አንቀጽ ስር የተመሰረተ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የመጀመሪያው በኃይል፣ በዛቻ፣ በአድማና ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ኢ-ሕገመንግስታዊ ምርጫ በማካሄድ በሕገ-መንግሥት የተቋቋመና እውቅና ያለው የክልል መንግስት መለወጥ ለማድረግ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል መቅጫ ሕግ አንቀጽ 238 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ መሆኑን አመልክቷል።
በሁለተኛ ክስ ደግሞ የፌደራሉን መንግሥት በኃይል ለመለወጥ በማሰብ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የፌደራል መንግሥትን በመሳሪያ ጥቃት መለወጥ የሚችል የትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ የተባለ የጦር ኃይል በማደራጀት በአገር መከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት በማድረስ፣ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1176/2011 አንቀጽ 3/1እና 3/2 በመተላለፍ ወንጀል መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
ዐቃቤ ሕግ በ62 ሰዎች ላይ ላቀረበው ክስ ለአስረጂነት 510 የሰው ምስክሮችን እና 5329 ገጽ የሰነድ ማስረጃዎችን በማያያዝ ጉዳዩን ለሚመለከተው ፍርድ ቤቱ ቅርቧል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕገ-መንግስትና የሽብር ወንጀሎችን የሚያየው አንደኛ ችሎት ክሱን በመዝገብ ቁጥር 27128102 በመቀበል በማረሚያ ቤት የሚገኙ ተከሳሾችን ማረሚያ ቤቱ እንዲያቀርብ ቀሪ ተከሳሾችን የፌዴራል ፖሊስ መጥሪያ አድርሶ እንዲያቀርብ በማዘዘዝ ለሐምሌ 26/2013 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን ገልጿል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የፌደራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በጥቃቱ ውስጥ እጃቸው አለበት ያለቸውን የቡድኑን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮችን ለመያዝ የሚያስችል የእስር ማዘዣ ማውጣታቸው ይታወሳል።
የፌዴሬሽንም ምክር ቤት የትግራይ ክልል መንግሥትን ሕገ ወጥ በማለት እንዲበተን ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የነበረውን ህወሓት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ብሎ ሰይሞታል።
ለስምንት ወራት ከተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ በኋላ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ክልል ሠራዊቱን ማስወጣቱን ያስታወቀ ሲሆን፤ የህወሓት ኃይሎች በበኩላቸው አብዛኛውን የክልሉን ክፍል መቆጣጠራቸውንና "ሕጋዊው የክልሉ መስተዳደር ወደ ቦታው ተመልሷል" ማለታቸው ይታወሳል።














