ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእስራኤል ፍልስጤም ግጭት የጦር ወንጀል እንደተፈፀመ አንድ ጥናት ይፋ አደረገ
የእስራኤል ፖሊስ እና የፍልስጤም ታጣቂዎች ባለፈው ግንቦት ጥቃት በፈፀሙ ወቅት የጦር ወንጀል የሚባሉ ጥሰቶችን ፈፅመዋል ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ይፋ አደረገ።
የመብት ተሟጋች ቡድኑ ባደረገው ጥናት መሠረት 62 ንፁሃንን የገደሉት ሦስት የእስራኤል ጥቃቶች ወታደራዊ ዒላማ እንደነበራቸው የሚያሳይ ማረጋገጫ አልተገኘም ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ጋዛ ውስጥ ያሉ ወታደራዊ ሥፍራዎችን ነው ዒላማ ያደረግኩት ይላል።
ዘገባው አክሎ የፍልስጤም ታጣቂዎች ወደ እስራኤል የተኮሷቸው 4300 ሮኬቶች ንፁሃንን ሳይለዩ ጥቃት አድርሰዋል ይላል።
ባለፈው ግንቦት ለ11 ቀናት በዘለቀው የእስራኤል ፍልስጤም ግጭት ቢያንስ 260 ሰዎች ጋዛ ውስጥ ሲገደሉ እስራኤል ውስጥ ደግሞ 13 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ቢያንስ 129 ጋዛ ውስጥ የተገደሉ ሰዎች ንፁሃን ዜጎች ናቸው ይላል።
የእስራኤል ጦር 200 ታጣቂዎችን ግድያለሁ ቢልም ጋዛን የሚቆጣጠረው ሃማስ ደግሞ 80 ተዋጊዎቹ እንደሞቱበት ተናግሯል።
የሂዩማን ራይትስ ዎች ጥናት በዋነኛነት ያጠነጠነው በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል ባላቸው ሶስት የእስራኤል ጥቃቶች ላይ ነው።
በፈረንጆቹ መጋቢት 10 ቤይት ሃኑን ላይ የእስራኤል ሚሳኤል ባደረሰው ጥቃት አራት መኖሪያ ቤቶችን ሲመታ ስምንት ሰዎች ደግሞ ተገድለዋል ይላል ጥናቱ። የእስራኤል መከላከያ ግን ፍንዳታው የተከሰተው በፍልስጤም ሮኬት ነው ይላል።
ግንቦት 15 በሻቲ ስደተኞች መጠለያ ላይ የተጣለ ቦምብ ሶስት ፎቆች ያሉትን ሕንፃ ያወደመ ሲሆን 10 ሰላማዊ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል ይላል ዘገባው።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በወቅቱ ከፍተኛ የሃማስ ባለሥልጣናት ሕንፃው ውስጥ ነበሩ ቢልም የዓይን እማኞች ግን ታጣቂዎችን አለማየታቸውን ይናገራሉ።
ሶስተኛው ጥቃት ግንቦት 16 ጋዛ ውስጥ የተፈፀመ ሲሆን ጥናቱ እንደሚለው ተከታታይ የአየር ጥቃቶች አል-ዋዳ መንገድ ላይ ያሉ ሶስት ሕንፃዎች እንዲፈርሱ አድርገዋል፤ 44 ሰዎች ደግሞ ተገድለዋል።
የእስራኤል ጦር ግን ታጣቂዎች ሲጓጓዙበት የነበረ ከመሬት በታች ያለን መንገድ ለመምታት እንጂ ሕንፃው ለማፍረስ የተደረገ ጥቃት አይደለም ይላል።
ጥናቱ በሶስቱም ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች አቅራቢያ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ የሚያሳይ ምንም ዓይነት መረጃ የለም ሲል ይጠቁማል።
የመብት ተሟጋች ቡድኑ አክሎ ሰላማዊ ዜጎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ጥንቃቄ ማድረግን ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠት ያስፈልጋል ሲል ፅፏል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ "ጥቃቶቹ ወታደራዊ ሥፍራዎችን ብቻ ዒላማ ያደረጉ ናቸው" እንዲሁም "ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥንቃቄ እናደርጋለን" ማለታቸውን ዘገባው አስነብቧል።
ማክሰኞ ዕለት የእስራኤል ጦር ኤኤፍፒ ለተሰኘው የዜና ወኪል "ሂዩማን ራይትስ ዎች ሃማስና ሌሎች ሽብርተኛ ድርጅቶች ወደ እስራኤል ከተማዎች ሮኬት በመተኮስ የፈፀሟቸውን ዓለም አቀፍ ሕግ የሚጥሱ ወንጀሎችን እንደመውቀስ ከዚህ በፊት መልስ የሰጠንበትን ወቀሳ ደግሞ ማምጣት መርጧል" ሲል ተናግሯል።
የመብት ተሟጋቹ ሃማስ የፈፀማቸውን ጥቃቶች የሚቃኝ የጥናት ዘገባ በሚቀጥለው ወር ይፋ እንደሚያደርግ አሳውቋል።
ሃማስ፤ "ምንም እንኳ የእስራኤል ጦር ጅምላ ጭፍጨፋ ቢፈፅምም በተቻለ መጠን ሰላማዊ ዜጎችን ላለማጥቃት ሞክረናል" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።