ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራቅ የኢድ ገበያ በደረሰ የቦምብ ጥቃት 25 ሰዎች ተገደሉ
በኢራቅ አንድ ጉሊት ውስጥ ለኢድ አረፋ ክብረ በዓል እየተገበያዩ የነበሩ 25 ሰዎች በቦምብ ጥቃት ተገደሉ፡፡
የቦምብ ጥቃቱ የደረሰው ዛሬ ማክሰኞ በሰሜን ሳድር ከተማ በርካታ ቤተሰቦች የአረፋ በዓልን ለማክበር ገበያ ወጥተው ሽር ጉድ በሚሉበት ሰዓት ነው፡፡
ይህ የቦምብ ጥቃት ባለፉት ስድስት ወራት ከደረሱ የቦምብ ጥቃቶች ሁሉ ብዙ ሰዎች የሞቱበት ነው ተብሏል፡፡ ከ25ቱ ሟቾች ሌላ በርካቶች ቆስለው ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡
የኢስላሚክ ስቴት ወይም በምሕጻሩ አይኤስ የሚባለው አሸባሪ ድርጅት ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነት ወስዷል፡፡ ‹ቦምቡን እንደ ቀበቶ ታጥቆ ገበያው ላይ ያፈነዳው የኛው አባል ነው› ሲል በኩራት መግለጫ ሰጥቷል፤ አይኤስ፡፡
በፈረንጆች 2017 መጨረሻ የኢራቅ መንግሥት የሱኒ ጂሐዲስቶች ቡድንን ድል አድርጊያለሁ ሲል አውጆ ነበር፡፡
ሆኖም ግን አሁንም ድረስ አልፎ አልፎም ቢሆን እነዚህ የሽብር ድርጅቶች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት ማድረሳቸው አልቀረም፡፡
አይ ኤስ በሚያዚያ ወር በሳድር ከተማ ገበያ ላይ በመኪና የተጠመደ ቦንብ ያፈነዳሁት እኔ ነኝ ብሏል፡፡ .
የሳድር ከተማ በብዛት የሺዓ ሙስሊሞች የሚኖሩባት ናት፡፡
ከዚህ ጥቃት ሌላ በጥር ወር በጣያራን አደባባይ 32 ሰዎችን የገደለውን ሌላ መንትያ የቦምብ ጥቃት ያቀነባበርኩት እኔ ነኝ ብሏል፤ አይኤስ፡፡
ይህን ጥቃት ተከትሎ የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል ካዲሚ የቦምብ ጥቃት የደረሰባት ከተማ የፌዴራል ፖሊስ አዛዥ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እንዲደረግበት አዘዋል ተብሏል፡፡