ኢራን ኃይል ይሆነኛል ብላ ያበለፀገችው ዩራኒየም ስጋት ፈጥሯል

ኢራን የበለፀገ ዩራኒየም ሜታል ማምረት ጀምራለች፤ ይህ ደግሞ ኒውክሌር መሣሪያ እንድታመርት ይረዳታል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ተቆጣጣሪ ድርጅት አስታውቋል።

ነገር ግን ኢራን ለዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዩራኒየም የማበለፅገው ለአንድ ምርምር የሚሆን ነዳጅ ለማምረት ነው ብላለች።

የብሪታኒያ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ ባለሥልጣናት ይህ የኢራን እርምጃ የ2015ቱን የኒውክሌር ስምምነት የሚንድ ነው የሚል ስጋት አላቸው።

ዩናይትድ ስቴትስ የኢራንን ድርጊት "ያልተጠበቀ ወደኋላ የወሰደ እርምጃ" ብላዋለች።

በፈረንጆቹ 2015 የተገባው ስምምነት የኢራን ኒውክሌር ፕሮግራም ላይ እግድ የሚጥል ሲሆን ሃገሪቱ መሣሪያውን እንዳታመርት ይከለክላል።

በምትኩ ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮፓ ሃገራት ኢራን ላይ የጣሉትን የምጣኔ ሃብት ማዕቀብ ለማንሳት ተስማምተው ነበር።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በ2018 አሜሪካን ከዚህ ስምምነት አስወጥተው ኢራን ላይ መልሰው ማዕቀብ ጥለው እንደነበር ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ ኢራን ስምምነቱን በተደጋጋሚ ስትጥሰው ቆይታለች።

የአሁኑ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እስካሁን ትራምፕ ኢራን ላይ የጣሉትን ማዕቀብ አልሻሩም።

ነገር ግን የአሜሪካና አውሮፓ ባለሥልጣናት ቪዬና ተገናኝተው ስምምነቱን እንደ አዲስ ተግባራዊ ለማድረግ እያቀዱ ይገኛሉ።

ተመራጩ የኢራን ፕሬዝደንት ኢብራሂም ራይሲ ሃገራቸው በስምምነቱ እንድትገዛና አሜሪካ ማዕቀቧን እንድታነሳ ይፈልጋሉ።

ማክሰኞ ዕለት በወጣ መግለጫ ዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ "ዛሬ ኢራን ዩራኒየም ኦክሳይድ 20 በመቶ ወደ ዩ-235 በልጽጎ ለምርምርና ዕድገት ለማዋል ኢስፋን ወደሚገኝ ቤተ ሙከራ ተልኳል ስትል አሳውቃናለች። ይህ ዩራኒየም እንደገና በልጽጎ ነዳጅ እንደሚሆን ገልፃለች" ብሏል።

የዩኬ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ ባለሥልጣናት ግን የኢራን ውሳኔ "ክፉኛ እንደሚያሳስባቸው" ተናግረዋል።

"ኢራን ዩራኒየም ሜታል ለማበልፀግ የሚያስግድዳት የተጠቃሚ ፍላጎት የላትም፤ ይህ ንጥረ ነገር ለኒውክሌር ግንባት ወሳኝ እርምጃ ነው" ሲሉ ሶስቱ ሃገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

መግለጫው አክሎ ኢራን ቪዬና ላይ እየተደረገ ወዳለው ውይይት እንድትመለስ ጠይቋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ምንም እንኳ እየተደረገ ያለው ውይይት መች እንደሚቋጭ ቀነ ቀጠሮ ባያስቀምጡም "ጊዜ በገፋ ቁጥር ኢራን የስምምነቱ አካል የመሆኗ ጉዳይን የምናየው ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል።