የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት የግብጽ የአክሲዮን ገበያ እንዲቀዛቀዝ ማድረጉ ተገለጸ

የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መጀመሩ የግብጽ አካክሲዮን ገበያ እንዲቀዛቀዝ ማድረጉ ተገለጸ።

የግብጽ ዋና የአክሲዮን ገበያ መረጃ ማክሰኞ ዕለት ሁለት በመቶ ያህል የቀነሰ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ ሁለተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት መጀመሩ ነው ተብሏል።

ትናንት ኢትዮጵያ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት መጀመሯ የተነገ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌት መጀመሯ የቀጠናውን መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ስትል እርምጃውን ግብጽ ታቅማ ነበር።

የግብጽ የመስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብደል አቲ ከኢትዮጵያ በኩል የውሃ ሙሌቱ ስለመጀመሩ የሚገልጽ ይፋዊ ደብዳቤ እንደደረሳቸው አመልክተው ውሳኔውን ግን አንቀበለውም ብለዋል።

እንደ ሮይተርስ የዜና ወኪል ከሆነ የግብጽ ዋና የአክሲዮን ገበያ መረጃ ጠቋሚ 10,155 ነጥቦችን ወይም 1.80 በመቶ ቀንሷል።

የስሪ ዌይ ብሮከሬጅ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ራኒያ ያኩብ "የሚከናወኑት የባለሀብቶች ግብይቶች የፍርሃት ናቸው። ከህዳሴው ግድብ [የውሃ ሙሌት] በስተቀር ለውድቀቱ ሌሎች ምክንያቶች የሉም" ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ እና ለህዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማቅረብ ወሳኝ ነው ስትል ግብጽ በበኩሏ ግድቡን ለውሃ አቅርቦቷ ከባድ ስጋት አድርጋ ትመለከተዋለች።

ግብጽ እንደ ሱዳን ሁሉ ከግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በፊት ኢትዮጵያ ወደ አስገዳጅ ስምምነት እንድትመጣ ጠይቃ ነበር።

የጸጥታው ምክር ቤት በግድቡ ጉዳይ በቅርቡ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።

የቤልቶን አክሲዮኖች 6 በመቶ ሲቀንሱ የፓዮኒየርስ ሆልዲንግ ደግሞ 4.9 በመቶ ቀንሷል። በተጨማሪም ኤል ስዊዲ ኤሌክትሪክ ሌላኛው የግብጽ ኩባንያ በ3.9 በመቶ እና ፋውሪ ደግሞ 3.1 በመቶ ቅናሽ አስመዝግበዋል፡፡