የትግራይ ኃይሎች ማንሰራራትና በኢትዮጵያ ላይ ያስነሳው ጥያቄ

የትግራይ አማፂያን ኃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከገደለውና በርካታ ሚሊዮኖችን ለምግብ እርዳታ ካጋለጠው የስምንት ወራት ጦርነት በኋላ የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን መቆጣጠራቸው እንደ ትልቅ እርምጃ እየተቆጠረ ነው።

ነገር ግን የትግራይ ኃይሎች መቀለን መቆጣጠር የጦርነቱን አቅጣጫ ይቀይረው ይሆን?

የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮቹን ከወራት ጦርነት በኋላ ማስወጣቱን ተከትሎ የመቀለ መንገዶች በደስታ ታጅበው ታይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መከላከያ ኃይሉ የወጣው መቀለ ከዚህ በኋላ "የስበት ማዕከል" ባለመሆኗ ነው ቢሉም ዘግይተው ደግሞ ወታደሮቹ የወጡት ተጨማሪ እልቂትን ለማስወገድ ነው ብለዋል።

"በጦርነቱ በጣም ወሳኝ የሆነ ለውጥ አይተናል" ይላል የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ነባር ተንታኝ ዊሊያም ዳቪሰን።

"ይህ የሚያሳየው ምናልባትም የፌዴራል መንግሥቱ መቀለን መቆጣጠር እንዳቃተው አሊያም ደግሞ ከትግራይ መውጣት አስፈላጊው ውሳኔ መሆኑን ማመኑን ነው። የሕወሓት ኃይሎች ወሳኝ የሚባሉ የጦርነት አምባዎችን ድል መንሳታቸው ሳይረሳ" ይላሉ ተንታኙ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮቹ ከወጡ በኋላ በትግራይ ክልል የተናጠል የሰብዓዊ እርዳታ ተኩስ አቁም አውጇል። መንግሥት ይህ ያስፈለገው የእርሻ ወቅት በመሆኑና የእርዳታ ሥራዎችን ማከናወን ለማስቻል መሆኑን ጠቁሟል።

ነገር ግን ከዚህ በኋላ የትግራይ ክልል ኃይሎች ጦርነታቸውን ቀጥለው ሽረን ጨምሮ በርካታ ከተሞችን ተቆጣጠረዋል።

አሁን የትግራይ ክልል አማፂያን በዚህ ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት የበላይነቱን የያዙ ይመስላል። ነገር ግን ወደፊት ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጊዜ የሚፈታው ነው።

በአማራ ክልል በኩል ያለው ነገር

ተንታኞች የኢትዮጵያ መሪ አሁን ትኩረታቸውን ወደ ምዕራባዊ ትግራይ አዙረው በትግራይ አማፂያንና በአማራ ክልል መካከል በሚኖረው ግጭት ላይ ያደርጋሉ ይላሉ።

በአማራና በትግራይ ክልል መካከል ያለው የድንበር ግጭት እንደሚቀጥል ይጠረጠራል። የአማራ ክልል በሕወሓት የበላይነት ወቅት ተወስደውብኛል የሚላቸውን መሬቶች ለማሸነፍ ይታገላል።

"የአማራ ብልፅግና ማለት በገዢው የዐቢይ ፓርቲ ውስጥ ካሉ ሁለት ፈርጣማ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው" ይላሉ የፕሮቴክሽን ግሩፕ ኢንተርናሽናል ተንታኝ ኢያን ማክዴርሞት።

"ስለዚህ ይህ ማለት የአማራ ክልል ከትግራይ ክልል ክፍሎች የኔ መሬቶች ናቸው የሚላቸውን እንዲወስድ እርዳታ ሊያደርጉ አሊያም ግጭቱን ሊታገሱ ይችላሉ" ይላሉ ተንታኙ።

ዳቪሰን ደግሞ የፌዴራል መንግሥቱ ወደ አማራ ክልል ትኩረቱን ሊያደርግበት የሚችልበት ሌላኛው ምክንያት ክልሉ ከሱዳን ጋር ድንበር የሚጋራ በመሆኑ ነው ይላል።

ተንታኙ አክሎ እንደሚለው ይህ የትግራይ ክልል ኃይሎች በሱዳን በኩል ዓለም አቀፍ የአቅርቦት መንገድ እንዳያገኙ ያደርጋል ይላል።

የሞራል ድቀት

አሁን ግልፅ ያልሆነው ነገር እንዴት የኢትዮጵያ ወታደር ባለፉት ስምንት ወራት ሊዳከም ቻለ የሚለው ነገር ነው።

አማፂያኑ በወርሃ ሰኔ በከፈቱት ጥቃት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን "ከአገልግሎት ውጭ" እንዳደረጉ ይናገራሉ።

ነገር ግን ይህን ሲሉ ወታደሮቹ ተገድለዋል አሊያም የጦርነት እሥረኛ ሆነው ተማርከዋል የሚለውን ግልፅ አላደረጉም። ቢሆንም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ የደረሰው ጥቃት ቀላል የሚባል አይመስልም።

የቦስተን ዎርልድ ፒስ ፋውንዴሽን ኃላፊ የሆኑት አሌክስ ደ ዋል፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት 20 ክፍለ ጦር የያዘ ሲሆን ሰባቱ ክፍለ ጦር ሙሉ በሙሉ ወድሟል ሶስት ክፍለ ጦር ደግሞ ተበታትኗል ይላሉ።

ነገር ግን ሌሎች ተንታኞች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ የደረሰው ጥቃትን ለመረዳት እጅግ አዳጋች ነው ይላሉ።

"ይህ የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ነው" የሚለው ዳቪሰን "መሬት ያለውን እውነታ ለመረዳት ቢያዳግትም ጦሩ ላይ የደረሰው ጥቃት የሚያሳስብ ነው። በጣም ከበድ ያለ የሞራል ሽንፈት ግን ደርሷል" ሲል ያክላል።

"ከዚህ ቀደም በቀጣናው በጣም የተከበረ የሰላም አስከባሪ ተደርጎ የሚታየው ጦር አሁን ላይ የተዳከመ ይመስላል" ባይ ነው ተንታኙ።

እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ነገር ይህ ጦርነት ኢትዮጵያን ከበድ ያለ የፋይናንስ (ገንዘብ) ጉዳት እንዳስከተለባት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ ክልል ባለው ጦርነት የኢትዮጵያ መንግሥት ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ አሊያም 2.3 ቢሊዮን ዶላር አውጥቷል ብለዋል።

ይህ በመልሶ ማገገምና በምግብ እርዳታ ላይ የወጣው ወጭ የሃገሪቱን ዓመታዊ በጀት 20 በመቶ የሚሸፍን ነው።

ከዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ የሚደርሰው ጫና

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀጣይ እርምጃዎች ለወራት ጦርነቱ እንዳሳሰበው ሲናገር በነበረው የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በንቃት የሚታዩ ነው የሚሆነው።

የፌዴራል መንግሥቱ ከመቀለ ከተማ ከወጣ በኋላ በትግራይ ክልል የኤልክትሪክ ኃይልና የመገናኛ መስመሮችን አቋርጧል ተብሎ እየተተቸ ይገኛል።

የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ በክልሉ ያሉ ሆስፒታሎች በጄኔሬተር ኃይል እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል ሲል የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ ይናገራል።

"ይህ የሰብዓዊ እርዳታ ተኩስ አቁም ሊሆን አይችልም፤ እንደውም የሰዓብዊ እርዳታውን ሊያደናቅፍ የሚችል ነው" ይላል ዳቪሰን።

"የኢትዮጵያ ፖሊሲ የሚመስለው አሁን ከተሸሸገበት የተመለሰው የቀድሞው የትግራይ አስተዳደር ትግራይን እንዳያስተዳድር ሁኔታዎችን ማበላሸት ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለሰላማዊው ማሕበረሰብ ቀጣይ አደጋ ነው።"

የባይደን አገዛዝን ጨምሮ ኃያላን የሚባሉቱ ሃገራት በትግራይ ባለው ግጭት ምክንያት አዲስ አበባ ላይ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።

ዋሺንግተን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሚሊዮኖች የምግብና ሌሎች እርዳታ መንገድ ሊከፈት ይገባል ትላለች።

ይህ ካልተሻሻለ "ኢትዮጵያና ኤርትራ ተጨማሪ ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል" ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ፀሐፊ ሮበርት ጎዴክ ተናግረዋል።

አክለው "በትግራይ ያለውን አሰቃቂ ሁኔታ እያየን ዝም አንልም" ብለዋል።

የኤርትራ ወታደሮች ሁኔታ

የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ቆመው ከጦርነት መባቻ ጀምሮ ሲዋጉ ነበር። ነገር ግን ጦርነቱ ሁለቱም ሃገራት ካሰቡት በላይ ጊዜ ወስዷል።

"አሁንም ትልቁ ጥያቄ የኤርትራ ወታደሮች መቼ ነው የሚወጡት የሚለው ነው" ይላሉ ደ ዋል።

ማክዴርሞት እንደሚሉት ጦርነቱ በሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደረ ይመስላል። "በአዲስና አስመራ መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል" ሲሉ ያክላሉ።

"የዐቢይ አስተዳደር የአማራ ኃይሎችን መግፋት እንደሌለበት ሁሉ ኤርትራንም መግፋት የለበትም። በዚህ ኦፕሬሽን ላይ ጉልህ ሚና ነበራቸውና።"

በአፍሪካ ቀንድ ለመሰል አለመረጋጋት አዲስ አይደለችም። ነገር ግን የኢትዮጵያ አለመረጋጋት ለቀጣናው ሌላ ቀውስ ሊያስከት እንደሚችል ስጋት አለ።

እስካሁን ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኃይል በእጃቸው አለ። ነገር ግን ይህን ኃይል ካጡት አደጋው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ይላል ዳቪሰን።

"የሃገሪቱ ሕልውና መናድ ይቅርና ሌላ ግጭት ከተነሳ ኢትዮጵያ በቀጣናው ካላት ድርሻ የተነሳ በጣም አደጋ ሊሆን ይችላል።"

"ቢሆንም ይህ አደጋ የሚቀር አይመስልም። ነገር ግን የዚህ አደጋ ትርፍ በትኩረት ማሰብ ያስፈልጋል" ባይ ነው ተንታኙ።

ትግራይ - መሠረታዊ መረጃዎች

  • ኢትዮጵያ በብሔር መስመር የተከፈሉና ራሳቸው የቻሉ 10 ክልሎች አሏት
  • በፈረንጆቹ 2018 በጊዜው የነበረው መንግሥት ላይ የደረሰውን ጫና ተከትሎ ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመው የለውጥ ሂደቶችን አራምደዋል
  • የትግራይ ክልል ፖለቲከኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማዕከላዊውን መንግሥት አቅም ሊያጠናክሩ ይሻሉ ሲሉ ይወቅሳሉ
  • ጦርነቱ የተጀመረው የፌዴራል መንግሥቱ የትግራይ ኃይሎች ባለፈው ኅዳር የሠራዊቱን ካምፕ አጥቅቷል ካለ በኋላ ነው
  • ጦርነቱ ከተጀመረ ከሳምንታት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጦርነት አብቅቷል ብለው ቢያውጁም ሰኔ ላይ በተካሄደው ምርጫ አካባቢ ግጭቱ እንደ አዲስ አገረሸ
  • የሕወሓት ታማኝ የሆኑ አማፂያን የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን ተቆጣጠሩ
  • ኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ ተኩስ አቁም አውጃለች፤ 350 ሺህ ሰዎች የረሃብ ቋፍ ላይ እንዳሉ እየተነገረ ነው