ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
30 ሺህ የትግራይ ህፃናት በሞት አደጋ ላይ ናቸው ተባለ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ በሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናትን በአስቸኳይ መድረስ ያስፈልጋል አለ።
የተባበሩት መንግሥታት ህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ እንዳለው 30 ሺህ የሚሆኑ ህፃናት የሞት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ገልጿል።
ህፃናቱን ከሞት አደጋም ለመታደግ አስፈላጊ ቁሶች ሊደርሱ ይገባል ብሏል።
ይህንንም ለማድረስ መንገዶች መከፈት አለባቸው እንዲሁም ሰብዓዊ ተኮር በረራዎች መፈቀድ አለባቸው በማለት በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።
"የቴሌኮም አገልግሎት ሊመለስ ይገባል፣ የመብራት አገልግሎትም እንዲሁ መቀጠል አለበት። በተጨማሪም የሰብዓዊ እርዳታን ለማቅረብ ህዝቡን ልንደርስ ይገባዋል" በማለት የዩኒሴፍ ተወካይ አዴሌ ክዶር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣን በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ሰራዊት የትግራይ ክልል መዲና መቀለን እንደገና መቆጣጠር እንደሚችል አስታውቋል። አስፈላጊም ከሆነ በሶስት ሳምንታት ብለዋል።
የትግራይ ኃይሎች ሰኞ እለት መቀለን ተቆጣጥረዋል።
ጦሩ የትግራይ አማፂ ኃይል ከዚህ በኋላ ችግር እንዳልሆነና አገሪቷ ለተደቀነባት ሌሎች ስጋቶች መዘጋጀት ስላለበት ነው ከተማዋን ለቆ የወጣው ብሏል።