ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመሐመድ አሊ የልጅ ልጅ የመጀመሪያውን ፕሮፌሽናል የቦክስ ውድድር ሊያደረግ ነው
የታዋቂው የቦክስ ስፖርት ኮከብ የመሐመድ አሊ የልጅ ልጅ የአያቱን ዱካ በመከተል በፕሪፌሽናል የውድድር ዘርፍ የመጀመሪያውን ውድድሩን ሊያደርግ መሆኑ ተነገረ።
ኒኮ አሊ ዋለሽ የአያቱን 27 የቦክስ ውድድሮችን ካዘጋጀው አሜሪካዊ የቦክስ ስፖርት አዘጋጅ ከሆነው ቦብ አረም ጋር ነው ለዚህ ውድድር የተፈራረመው።
አሊ ዋልሽ "አያቴ የጀመረውን የቦክስ ውርስ በማስቀጠሌ ክብር ይሰማኛል" ብሏል። ጨምሮም "እንደ ቀላል የማልመለከተው ኃላፊነት ነው።"
መሐመድ አሊ ለሦስት ጊዜያት የዓለም ከባድ ሚዛን የቦክስ ውድድር አሸናፊ ሲሆን በስፖርቱ ውስጥ ዝና እአአ በ 1999 የቢቢሲ ስፖርት የምዕተ ዓመቱ ስፖርተኛ ሆኖ ተመረጦ ነበር።
'ታላቁ' በመባል የሚታወቀው አሊ እአአ በ2016 ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ፓርኪንሰን በተባለው በሽታ ሲሰቃይ ቆይቷል።
የ89 ዓመቱ የቦክስ ስፖርት አወዳዳሪ ቦብ አሩም በአሜሪካ ውስጥ የከፍተኛ ደረጃ ማስተዋወቂያ ዘርፉን የሚመራ ሲሆን የአሊን ግጥሚያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው እአአ በ1966 ነው።
በላስ ቬጋስ ቢሮው ውስጥ ሁለቱም ፊርማቸውን ያኖሩበትና ከመሐመድ አሊ ጋር የተነሱት ትልቅ ፎቶ ተሰቅሏል።
የአሩም መልዕክት "ሁሉንም እንዲቻል ላደረገው መሐመድ በፍቅር" የሚል ጽሑፍ ይነበባል።
"የኒኮ አያት ጥሩ ተጋጣሚ ነበር" ይላል አሩም።
"ከብዙ ዓመታት በኋላ የልጅ ልጁን የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ግጥሚያ እናስተዋውቃለን ብሎ ማን ያምን ነበር?"
"ኒኮ የአያቱን ስኬት እንደሚደግም ተስፋ እናደርጋለን። ከመሐመድ አሊ የልጅ ልጅ የሚጠብቅ ታላላቅ ባህሪያት ያለው ወጣት ነው" ሲል መስክሯል።
ኒኮ አሊ ዋልሽ እካሁን ወደ 30 የሚሆኑ አማተር የቦክስ ስፖርት ግጥሚያዎችን አድርጓል።
መሐመድ አሊ ማን ነው?
መሐመድ አሊ ዝናው ጣራ በነካበት ወቅት በምድር ላይ በጣም ታዋቂ ሰው ነበር ማለት ይቻላል።
"እኔ ታላቅ ነኝ" ለሚለው አሊ በዓለም ከባድ ክብደት የቦክስ ሻምፒዮና ላይ ሦስት ጊዜ ማሸነፉን ማን ሊጠራጠር ይችላል።
ለሲቪል መብቶች በግልጽ ያደረገው ድጋፍ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተከታዩ እንዲሆኑ አድርጓል።
ጥር 17/1942 ሉዊስቪል ኬንታኪ ውስጥ የተወለደው መሐመድ አሊ የመጀመሪያ ስሙ ካሲየስ ማርሴለስ ክሌይ ነበር።
በአጭር ጊዜ ስልጠና እአአ በ1954 የአማተር ፍልሚያ በማድረግ የውድድር ጉዞውን 'ሀ' ብሎ ጀመረ።
ክሌይ በፍጥነት ወደ ቦክስ ስፖርት መድረክ ገባ ፣ በ1954 በሦስት ደቂቃ አማተር ፍልሚያ ተወዳዳሪነቱን ለመጀመሪያ ጊዜ አደረገ።
በኋላ ላይ ማርቲን "ከአብዛኞቹ ወንዶች ልጆች የበለጠ ቆራጥ አቋም ስላለው ጎልቶ ወጣ" ብለዋል። እሱ እስካሁን ካሰለጠንኳቸው ከየትኞቹም ልጆች በጣም ታታሪ ስፖርተኛ ነበር" ብሏል።
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ከፍተኛ ደረጃ በመድረስ እአአ በ1959 የወርቅ ጓንት ሻምፒዮናነትን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል።
በ1960 ለሮም ኦሊምፒክ በአሜሪካ ቡድን ውስጥ ተመረጠ። መጀመሪያ ላይ ለመብረር በመፍራት ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆነም። በመጨረሻም ፓራሹት ገዝቶ በመልበስ ወደ ሮም ጉዞውን አድርጓል።
እዚያም በኦሊምፒክ የቦክስ ውድድር የቀላል ክብደት ሻምፒዮን ለመሆንም በቃ።
በ61 ግጥሚያዎች ላይ የተካፈለው መሐመድ አሊ በ56ቱ አሸናፊ ለመሆን ችሏል።
በቦክስ ታሪክ በቀዳሚነት የሚቀመጠው መሐመድ አሊ እአአ በ2016 ስኮትስዴል አሪዞና ውስጥ ነበር በ74 ዓመቱ ያረፈው።