ኮሮናቫይረስ: 'ልጆቼ እናታቸው በኮቪድ እንደሞተች ስለማያውቁ ትመጣለች ብለው ይጠብቃሉ'

ሕንድን ያመሰው ሁለተኛው የኮቪድ ሞገድ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን የማይነገር ሃዘን ጥሎባቸዋል። መከራ፣ ቸልተኝነት፣ አለመዘጋጀት እና በደንብ ያልታሰበበት የክትባት ዕቅድ ለብዙዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።
አልቱፍ ሻምሲ ሐዘንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕንዳውያ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ከገጠማቸው ልብን የሚሰብር ሐዘን መካከል አንዱ ነው።
ሚያዝያ መጀመሪያ ላይ ቤተሰቤ እንደተለመደው ደስተኛ ነበር። እኔና ባለቤቴ ሪሃብ ሦስተኛ ልጃችንን እየጠበቅን ነበር።
የማህጸን ሐኪሟ ከሚያዝያ 22 በፊት ሆስፒታል እንድንመጣ መክሮናል። ሪሐብ በእርግዝናዋ 38ኛ ሳምንት ውስጥ ስለነበረች በሚቀጥለው ቀን ለማዋለድ ነበር ዕቅዱ።
ነፍሰጡር ሴቶች ከመውለዳቸው በፊት ኮቪድ እንዲመረመሩ መመሪያ ወጥቷል። ተመረመረች። ኮሮና እንዳለባት ስናውቅ ደነገጥን። ሆስፒታሉ ኮሮና ያለባቸውን አይቀበልም። ሪሃብ ጊዜ ስለነበራት ሐኪሟ ሌላ ቀጠሮ ሰጠን። ኮቪዱ ላይ እንድናተኩርም ነገረችን።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ሪሃብ ከፍተኛ ትኩሳት አጋጠማት። ሚያዝያ 28 በሐኪሟ ምክር መሠረት የኮቪድ ህክምና ወደሚሰትበት ሆስፒታል አስገባናት።
ሆስፒታል ከገባች ሁለት ቀን ሆናት። ሪሃብ ጠንካራ መድኃኒት እየወሰደች በመሆኑ ህጻኑን እንደምናጣ ሐኪሙ ነገረን። አመሻሹ ላይ ህመሟ ተባብሶ የኦክስጂን ድጋፍ አስፈለጋት። ዶክተሮችም ህጻኑን በድንገተኛ ቀዶ ጥገና እንዲወለድ ወሰኑ።
ሆስፒታሉ በከፍተኛ ደም መፍሰስ ምክንያት እስከሞት የሚደርስ ከፍተኛ ዕድል እንዳለ የሚገልጹ ሰነዶችን እንድንፈርም አደረገ። ከገደል አፋፍ ዘሎ በሠላም የማረፍ ተስፋ ዓይነት ነው።
ከቀዶ ጥገናው በኋላ ሪሃብ ከፍተኛ የህክምና ክትትል ስለሚያስፈልጋት ሌላ ሆስፒታል የጽኑ ህሙማን አልጋ እንድፈልግ ተነገረኝ። የተሟላ የኮቪድ ህክምና ቢያስፈልጋትም እነሱ ሊያሟሉ አልቻሉም።
በዚህ ጊዜ ልጅ እንደወለድን ረስቻለሁ። በአዕምሮዬ የሚመላለሰው ብቸኛው ነገር ሪሃብን ማዳን ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለቀዶ ህክምናው አእምሮዬን እያዘጋጀሁ እያለ መጥፎ ዜና መጣ። ባለቤቴ ኮሮና እንዳለበት ያወቅነው አባቴም ዴልሂ በሚገኝ ሌላ ሆስፒታል የገባ ጊዜ ሲሆን ጤንነቱ እያሽቆለቆለ ነበር።
እናቴም ኮሮና የተገኘባት ሲሆን በአነስተኛ የኦክስጂን ድጋፍ በቤት ውስጥ ነበረች። ባለቤቷ እና የልጇ ሚስት ህይወታቸውን ለማትረፍ እየታገሉ እንደሆነ እንኳን አታውቅም።
ዓለም በዙሪያዬ ሊፈርስ ከጫፍ የደረሰ መሰለ። እንዲድኑ እየጸለይኩኝ የጽኑ ህሙማን አልጋ ፍለጋዬን አጧጡፍ ጀመር።
ሚያዝያ 29 ሴት ልጄ ተወለደች። አልጋ ማግኘት ስላልቻልኩ ሪሃብ ወደ ጊዜያዊ የጽኑ ህሙማን ክፍል እንድትዛወር ተደረገ።
ሆስፒታሉ በቂ ነርሶች አልነበሩትም። እኔም በኮሮና ተያዝኩኝ። የራሴን ትቼ ከሪሃብ ጎን ለመቆም ወሰንኩ። ስለመድኃኒቷ ያለማቋረጥ ነርሶችን ማሳሰብ ነበረብኝ።
እነሱ ደግሞ ወደ ሌላ ቦታ እንድወስዳት በተደጋጋሚ ይነግሩኛል። አጋዥ መተንፈፈሻ መሣሪያ (ቬንትሌተር) ያለው አልጋ ካገኘሁ በሚል የማውቃቸው ሰዎች ሁሉ ጋር ደዋወልኩኝ።
በመጨረሻም የየጽኑ ህሙማን አልጋ አገኘሁላት። እሷን የሚወስዳት የህይወት ድጋፍ መሣሪያ ያለው አምቡላንስ ግን አልነበረም። ሆስፒታሉ ህክምናውን እንዲቀጥልላት ተማጸንኩኝ። እነሱም እሷን ለማዳን የቻሉትን ሁሉ አደረጉ።
ግንቦት አንድን መቼም አልረሳውም። በርካታ ሆስፒታሎች ከፍተኛ የኦክስጂን እጥረት እንደገጠማቸው ይገልጹ ነበር። ሪሃብ የምትታከምበት ሆስፒታል ያሉ ሠራተኞችም ኦክስጂን ሊያልቅባቸው እንደሆነ ነግረውኝ ሲሊንደሮችን እንዳዘጋጅ ጠየቁኝ።
አመሻሹ ላይ አባቴ ከሚታከምበት ሆስፒታል ተደውሎልኝ ጤንነቱ በፍጥነት እያሽቆለቆለ እንደሆነ ተነገረኝ። እዚያ ስደርስ አባቴ ህይወቱ አልፏል።
ደንዝዤ ነበር። አስከሬኑን እያየሁ ከሪሃብ ሆስፒታል ስለኦክስጅን እጥረት የሚደርሰኝን መልዕክት እያነበብኩ ነበር። እናቴም በጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለችም። የሰባት እና የአምስት ዓመት ሴት ልጆቼ እናታቸው እና አዲሷ እህታቸው ቃል በተገባው መሠረት ለምን ቤት እንዳልመጡ ይጠይቁ ነበር።

ለእናቴ የ42 ዓመት የትዳር አጋሯን ሞት መንገር ከባድ ነበር። እሱ የቤተሰቡ ጠባቂ ነበር። የእሱ ማለፍ የበለጠ ተጋላጭ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አደረገኝ።
እሱን ቀብሬ በፍጥነት ወደ ሪሃብ ሆስፒታል ተመለስኩ። የእሷም ጤንነት አሽቆልቁሏል።
በቀጣዮቹ 11 ቀናት በተስፋ እና በተስፋ መቁረጥ መካከል ስወዛወዝ ቆየሁ። ሪሃብ በየቀኑ በመጠኑ እየተሻላት እንደሆነ ቢነገረኝም በከፋ ሁኔታ ውስጥ ነበረች።
ከሁለት ቀናት በኋላ ኩላሊቶቿ ድጋፍ አስፈለጋቸው። በማሽን የተደገፈ የደም እጥበት [ዲያሊሲስ] ጀመረች። የኦክስጂን መጠኗ መሻሻል ሲጀምር ከህክምና ክፍሉ እንድወጣ ተነገረኝ። ከሁለት ቀን በኋላ ቬንትሌተሩን ሲነቅሉላት እንደማያት ተነግሮኛል።
የዚያኑ ዕለት ምሽት 2 ሰዓት ገደማ ሪሀብን እንድትንከባከብ የቀጠርኳት የግል ነርስ ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለች ነገረችኝ። እናቴን እና ሴት ልጆቼን ለማየት ወደ ቤት ተመለስኩኝ።
ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ ከሆስፒታሉ ተደውሎ በፍጥነት እንድመለስ ተጠራሁኝ። ተጣድፌ ሆስፒታል ስደርስ ልቤ በአፌ ልትወጣ ደረሳ ነበር። ሪሃብ ግን በህይወት አልቆየችኝም።
የሆስፒታሉ ሠራተኞች "የልብ ችግር" እንደነበር ነግረውኛል። ሙሉ በሙሉ ተሰበርኩኝ። እኔ ጠንካራ ለመሆን እየሞከርኩ ነበር። ቤተሰቦቼን ተንከባክቤ በሚቀጥለው ቀን ባለቤቴን ለማየት እና ላወራት ተስፋ አድርጌ ነበር። ሊደረመስ ከቋፍ ደርሶ የነበረው ዓለሜ ፈረሰ።
የነበረኝ ብቸኛው ጭንቀት እናታቸው ወደ ቤት መቼም እንደማትመለስ ለልጆቼ እንዴት እንደምነግራቸው ነው። እስካሁንም አልነገርኳቸውም። እንዴት ማድረግ እንዳለብኝም አላውቅም። በየቀኑ ስለ እሷ ይጠይቁኛል። አሁንም ሆስፒታል መሆኗን እነግራቸዋለሁ። እህቴ አዲሷን ሕፃን በመጠበቅ እየረዳችኝ ነው።
ሪሃብ አስደናቂ ሴት ብቻ አይደለችም። አፍቃሪ እና አሳቢ እናት፣ ሚስት፣ ሴት እና ምራትም ነበረች። ደፋር እና በራስ መተማመን የነበራት ስለነበረች ነው የታገለችው።
አዲስ የተወለደችውን ልጃችንን ለማየት አልታደለችም። የሪሃብ ስጦታ አድርጌ ስለምወስዳት እንከባከባታለሁ። ለልጆቼ አባት እና እናት ለመሆን እየሞከርኩ ነው። ሪሃብ በህይወታችን የፈጠረችው ክፍተትን ግን በጭራሽ መሙላት አልችልም።
እሷን ለማዳን ከዚህ በላይ ማድረግ የምችለው ሌላ ነገር ይኖር ይሆን? እያልኩ አስባለሁ። የተሻለ ሆስፒታል ባገኝ ኖሮ በህይወት ትኖር ነበር? እላለሁ።
ቀላል መልሶች የሉትም። በእርግጠኝነት ግን የኮቪድ ክትባቶች እንደ ሪሃብ ያሉ ብዙ ሴቶችን ማዳን ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ክትባት ብታገኝ ኖሮ በሕይወት ትኖር ይሆናል። ለእርሷ ምንም ክትባት አልተገኘም።
በከባድ የኮቪድ በሽታ ለተያዙ እርጉዝ ሴቶች መንግሥት ክትባቱን ገና አላጸደቀም።
የህይወቴን አንጸባራቂ ብርሃን አጥቻለሁ። ባለፍኩበት መንገድ ሌላ ሰው እንዲያልፍ አልፈልግም።
በሌኛው ዓለም እስከማይሽ ደህና ሁኚ ሪሃብ።













