ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካዋ ግዛት ካሊፎርኒያ በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገገች
በአሜሪካ ደቡብ ምዕራብ ክፍሎች አደገኛ የተባለ ከፍተኛ ሙቀት መመዝገቡን ተከትሎ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሥርዓት ላይ የተፈጠረውን ስጋቶች ለመቅረፍ የካሊፎርኒያ ግዛት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገገች።
ከመጠን በላይ የሆነ የሙቀት ማስጠንቀቂያ በአሪዞና፣ በካሊፎርኒያ፣ በኔቫዳ እና በዩታ ግዛቶችም ለነዋሪዎች ተሰጥቷል።
በእነዚህ አካባኢዎች ነዋሪዎች ከፀሐይ ርቀው የአየር ማቀዝቀዣ መሳሪያዎች ባሉባቸው ስፍራዎች እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል።
የካሊፎርኒያ ነዋሪዎች ሙቀቱ ከፍተኛ ሆኖ እስከ እሁድ ድረስ ስለሚቆይ ኃይልን እንዲቆጥቡም ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
የግዛቲቱ ገዢ ጋቪን ኒውስም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ "በኃይል መሠረተ ልማት ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ እና የኃይል አቅርቦት አቅምን ለማሳደግ" ያለመ ነው ብለዋል።
በዓለም ላይ በጣም ሞቃታማ ከሆኑት ቦታዎች አንዱ በሆነው በካሊፎርኒያ ዴዝ ቫሊ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኝ ቴርሞሜትር ሐሙስ ዕለት 130 ፋራናይት ወይም 54 ዲግሪ ሴሊሺየስ ሙቀት መዝግቧል።
በዴዝ ቫሊ መደብር የምታስተዳድረው እና አብዛኛውን ህይወቷን በአካባቢው የኖረችው ዊሎ አልፎርድ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገረችው "የሙቀት መጠኑ እስከ 120 ፋራናይት ወይም 49 ዲግሪ ሴሊሺየስ ከሆነ ጥሩ ነው። ከፍ ካለ ግን የእውነት ይከብዳል" ብላለች።
ሙቀቱ የሳን ፍራንሲስኮ ቤይ አካባቢ ድረስ መስተዋሉን እና በአካባቢው በርካታ ከተሞች የማቀዝቀዣ ማዕከላት አቋቁመዋል።
በፊኒክስ አሪዞና ሐሙስ ዕለት ሙቀቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተነግሯል። በተመሳሳይም በላስ ቬጋስ እና በዴንቨር ለተከታታይ ለሦስተኛ ቀን ሙቀቱ ከተለመደው በላይ አሻቅቦ ተመዝግቧል።
በደቡብ ምዕራብ የአሜሪካ ክፍል የሚገኙ ወደ 50 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከመጠን በላይ የሆነው ሙቀት ጉዳት ያደርስባቸዋል በተባሉ ቦታዎች ይኖራሉ።
"የሙቀቱ ሞገድ በምዕራቡ አካባቢ [በባህር ዳርቻው] እየተባባሰ ነው ምክንያቱም አሸዋው ደርቋል" ሲሉ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት እና የእሳት አደጋ ባለሙያ የሆኑት ፓርክ ዊሊያምስ ለአሶሺዬትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
"በጋው ከመጠናቀቁ በፊት ተመሳሳይ ሁለት፣ ሦስት፣ አራት ወይም አምስት የሙቀት ሞገድ ሊኖሩን ይችላሉ" ብለዋል።