የቡድን 7 አገራት ዓለም አቀፍ የጸረ ወረርሽኝ እቅድ ይፋ ሊያደርጉ ነው

የቡድን 7 አባል አገራት ኮሮናቫይረስ ያሳደረው አይነት ጫና ከዚህ በኋላ በዓለም ላይ እንዳይደገም እርምጃ እንደሚወስዱ አስታወቁ።

በኮርንዎል ውይይት እያደረጉ ያሉት አገራቱ፤ ዓለም እንደ ኮሮናቫይረስ ያለ መሰናክል እንዳይገጥማት ምን አይነት እርምጃ እንደሚወስዱ በቀጣይ ይፋ ያደርጋሉ።

ከነዚህ መካከል የበሽታውን መከላከያ ክትባት ከ100 ቀን በታች ማምረት መቻል ይገኝበታል።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን "ከ2008 የፋይናንስ ቀውስ መማርና እኩልነት እንዲሰፍን መስራትም አለብን" ብለዋል።

ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ጣልያን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካን የያዘው ቡድን 7፤ ሰብዓዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ የሚያስከትል ክስተትን ለመከላከል ነው እቅድ የሚያወጣው።

በመላው ዓለም ከ175 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል። 3.7 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ መሞታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ያሳያል።

እቅዱ ምንድን ነው?

ማንኛውም በሽታ ሲከሰት ሕክምና ለመስጠት ወይም ክትባት ለመሥራት የሚወስደውን ጊዜ ከ100 ቀናት በታች የማድረግ እቅድ ተይዟል።

በመላው ዓለም የተቀናጀ የጤናና የዘረ መል ክትትል ማድረግ እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅትን አቅም ማጎልበትም ተጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ውጤታማ ክትባቶች ተሠርተው እየተሰራጩ ቢሆንም፤ በቀጣይ ግን መሰል ወረርሽኞች ከመሰራጨታቸው በፊት መግታት ያስፈልጋል ብለዋል።

"ወረርሽኙ ተከስቶ ካሳለፍናቸው 18 ወራት ተምረን በቀጣይ የተሻለ እርምጃ መውሰድ አለብን" ሲሉም ተናግረዋል።

የቡድን 7 አገራት እቅዱን ሲያወጡ በተለያየ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችንና የሳይንስ ተቋማትን አማክረዋል።

እቅዱ ይፋ ሲደረግ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም እና የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አምቶኒዮ ጉቴሬዝ ይገኛሉ።

ዶ/ር ቴድሮስ "እንደዚህ አይነት ወረርሽኞችን ለመከላከል ዓለማችን ጠንካራ የጤና ዘርፍ ክትትል ያስፈልጋታል" ብለዋል።

ክትባትን ለአገራት የማዳረስ ሥራ

ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ እንዳሉት፤ ዩኬ በሚመጣው ዓመት ከ100 ሚሊዮን በላይ ክትባቶችን ለድሃ አገራት ትደጉማለች።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በበኩላቸው፤ 500 ሚሊዮን የፋይዘር ክትባት ለ92 አገሮች እንሰጣለን ብለዋል። ይህም አፍሪካ ሕብረትን እንዲሁም መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮችን ያካትታል።

ሆኖም ግን ዩኬ ያወጣችው የክትባት እርዳታ እቅድ እየተተቸ ነው። ክትባቱ የሚደርስበት ፍጥነትና የሚከፋፈለው ክትባት መጠን ላይ ብዙዎች ጥያቄ አንስተዋል።

የቡድን 7 አባል አገራት በቀጣዩ ዓመት መጨረሻ አንድ ቢሊዮን ክትባት ለመለገስ ቃል ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው፤ እስከ 70 በመቶ የዓለም ሕዝብን ለመከተብ 11 ቢሊዮን ብልቃጥ ክትባት ያስፈልጋል።