ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤልሀን ኦማር እስራኤልን 'ይተቻል' የተባለውን ንግግሯን ተከላከለች
የአሜሪካዋ የኮንግረስ አባል ኤልሀን ኦማር እስራኤልን በተመለከተ ስላደረገችው ንግግር ከዴሞክራቶች የቀረበባትን ጥያቄ አጣጥላለች።
የኤልሀን የሥራ አጋሮች የሆኑ የአይሁድ ተወላጆች ስለ ንግግሩ ማብራሪያ ለማግኘት ቢጠይቁም ኤልሀን ግን እምብዛም ቦታ አልሰጠቻቸውም።
ኤልሀን እስራኤልን የሚተች ንግግር አድርጋ ከዴሞክራት ፓርቲ አጋሮቿ ጋር ውዝግብ ውስጥ ስትገባ የመጀመሪያዋ አይደለም። እአአ በ2019 ለእስራኤል የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነ የሚጠቁም ንግግር ካደረገች በኋላ ይቅርታ ጠይቃለች።
ኤልሀን ሰኞ በለጠፈችው ትዊት "ለማሰብ የሚከብዱ ጭካኔዎች በአሜሪካ፣ ሀማስ፣ እስራኤል፣ አፍጋኒስታን እና በታሊባን ተፈጽመዋል" ብላለች።
ጥፋተኞች እንዲጠየቁና ጥቃት የደረሰባቸው ፍትሕ እንዲያገኙም ጠይቃለች።
ለውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበችውን ጥያቄ ከዚህ ትዊት ጋር አያይዛ አውጥታለች።
ኤልሀን እስላማዊ ታጣቂዎቹ ሀማስ እና ታሊባንን በጠቀሰችበት ትዊት አሜሪካ እና እስራኤልም መካተታቸው ከሥራ አጋሮቿ ጥያቄ አስነስቶባታል።
የኒው ዮርኩ ዴሞክራት ጄሪ ናድለር የሚመራው ቡድን "አሜሪካ እና እስራኤል፤ ከሀማስ እና ታሊባን እኩል መታየታቸው ያስቆጣል። የተሳሳተም ነው" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
"በሕግ የበላይነት የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እና የሽብር ቡድን ያላቸውን ልዩነት ያምታታ ነው" ይላል መግለጫው።
ትውልደ ሶማሊያዊቷና ለኮንግረስ በመመረጥ የመጀመሪያ ከሆኑ ሙስሊሞች አንዷ የሆነችው ኤልሀን፤ ይህንን መግለጫ ያወጣውን ቡድን "አሳፋሪ" ብላ ገልጻለች። "ሙስሊም ጠል ስብስብ" ስትልም ወንጅላቸዋለች።
"ሌላ ጊዜ የኔን ድጋፍ ሲፈልጉ የሚደውሉልኝ የሥራ ባልደረቦቼ አሁን ግን ማብራሪያ ስጪን ለማለት መግለጫ ማውጣታቸው ያሳፍራል" ስትል ትዊት አድርጋለች።
ጨምራም "ይህ ሙስሊም ጠል ቡድን ያወጣው መግለጫ አስቀይሞኛል። መግለጫው ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት ሰዎች ድምጼን ለማፈን የሚያደርጉት ጥረት ከአቅም በላይ ነው" ብላለች።
'ስኳድ' በሚል የሚታወቁትና ከኤልሀን ጋር ጥምረት ያላቸው ሦስት የኮንግረስ አባላት ኤልሀንን ደግፈዋል።
አሌክሳንድርያ ኦካስዮ ኮርቴዝ የድጋፍ ድምጽ ካሰሙት አንዷ ናት።
"ሆነ ተብሎ የኤልሀንን ስም ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት ያሳዝናል። በግል መነጋገር የሚቻል ነገርን ዜና እንዲሆን ማድረግ ያለው ጉዳት አይታያቸውም" ብላለች።
ኤልሀን ባወጣችው መግለጫ፤ አንቶኒ ብሊንከን ለዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ያቀረቡትን ዝርዝር በተመለከተ ጥያቄ እንደምታነሳ አስታውቃለች።
ኤልሀን እስራኤልን በተመለከ ያላትን አቋም የሚጋሩ የምክር ቤት አባላት ቢኖሩም፤ ንግግሮቿን አዘውትረው የሚተቹም ጥቂት አይደሉም።
ኤልሀን ባደረገችው ንግግር አገራትን የጠቀሰችው አንዳንድ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ጉዳዮችን በማጣቀስ እንደሆነ ተናግራለች።
ዴሞክራቶች እስራኤል እና ፍልስጤምን በተመለከተ ያላቸው አቋም ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየተለወጠ መጥቷል። ሀዘኔታቸውን ከእስራኤል ይልቅ ወደ ፍልስጤም እያዘነበለ ነው።
ሆኖም ግን አሁንም የእስራኤል ፖሊሲ የሚደግፉ የኮንግረስ አባላት አሉ።
ኤልሀን በበኩሏ "የተናገርኩት አንዳንድ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ያሉ ጉዳዮችን በመጥቀስ ተጠያቂነትን ስለማስፈን ነው። የሽብር ቡድኖችን ከዴሞክራሲያዊ አገሮች ጋር እኩል አላደረኩም" ስትል ስለ ንግግሯ አብራርታለች።