ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይና ተማሪዎች ተቃውሟቸውን ለመግለፅ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቱን አገቱ
የቻይና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚያገኙት ዲግሪ ደረጃው ሊወርድ ይችላል በሚል ፍራቻ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቱን ማገታቸውን የቻይና ፖሊሰ አስታውቋል።
ናንጂንግ የተባለው ስመ ጥር ኮሌጅ ከአንድ የሙያ ተቋም ጋር ይጣመራል በሚልም ነው ተቃውሞው የተነሳው።
የሙያ ተቋሙ ይህ ግባ የማይባል በመሆኑ ተማሪዎቹ የሚያገኙት ዲግሪ የረከሰ ይሆናል በሚልም ነው ተቃውሞው ተቀጣጠለው።
ፖሊስ የተማሪዎቹን ተቃውሞ ለመበተን አስለቃሽ ጋዝና ዱላ የተጠቀመ ሲሆን አንዳንድ ተማሪዎች መጎዳታቸውም ሪፖርት ተደርጓል።
ከዚህም በተጨማሪ የዳንያንግ ከተማ ፖሊስ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ የናንኒንጅግ ኖርማል ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተሰባስበው የ55 አመቱን የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቱን ማገታቸውን ነው።
ግለሰቡን ለ30 ሰዓታት ያህልም አግተውት ነበር ተብሏል።
ተማሪዎች በመሳደብና የፀጥታ ኃይሎች እንዳይገቡም እክል ፈጥረው እንደነበር ተገልጿል።
ባለስልጣናቱ የተቋማቱ መጣመር ቀርቷል ቢሏቸውም ተማሪዎቹ ፕሬዚዳንቱን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆናቸውንም ፖሊስ በመግለጫው አትቷል።
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ፖሊስ ዱላና አስለቃሽ ጋዝ ሲጠቀሙ የሚያሳዩ ፎቶዎች አጋርተዋል። አንዲት ሴት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ጭንቅላቷ ላይ ደም እየፈሰሳት የሚያሳይ ፎቶ መውጣቱንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።
ፖሊስ በበኩሉ "የካምፓሱን የፀጥታ ሁኔታ ለመመለስ የፀጥታ ኃይሎች ህጉን ተከትለው አስፈላጊ ነው የሚባሉ እርምጃዎችን ወስደዋል። የታገተውንም ሰው ማስለቀቅ ችለዋል። እንዲሁም የተጎዱት ተማሪዎች ለህክምና ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል" ብሏል በመግለጫው
በርካቶች ፖሊስ ያልተገባ ኃይል ተጠቅሟል በሚል ተቃውሟቸውን ዌይቦ በተባለው ማህበራዊ ትስስር ገፅ እያሰሙ የነበረ ቢሆንም በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ የተቃውሞው ሃሽ ታግ እንዲታገድ ተደርጓል።
ነገር ግን በትዊተር ላይ የወጡ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት በሺዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በፖሊስ ተከበው ሲዘምሩ እንዲሁም ወደ በኋላም ፖሊስ ሲያሯሩጣቸውና አንዳንዶቹንም ሲጎተቱ ታይቷል።